2015 ኤፕሪል 4, ቅዳሜ

ስነ ልቦናዊ ሂስ

ስነ ልቦናዊ ሂስ በ “ራህማቶ” ረጅም ልቦለድ
መግቢያ
በዚህ አጭር ጽሑፍ የስነ ልቦናዊ ሂስ ምንነት፣ የስነ ልቦናዊ ሂስ መርሆዎችና የመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ። በአሰፋ ጉያ በ2002 ዓ.ም የታተመዉን “ራህማቶ” የተሰኘዉን ረጅም ልቦለድ መጽሐፍም ከተለያዩ የስነ ልቦናዊ ቲወሪዎች አንፃር ለመገምገም ሙከራ ይደረጋል። የመጽሐፉን አጽመ ታሪክ በማዉጣትና በታሪኩ ላይ የቀረቡ መረጃዎችን በመጠቀም የገጸ ባህሪያት ስነ ልቦና እንዴት እንደቀረበ ለመፈተሽ ሙከራ ይደረጋል። በመጨረሻም ከመጽሐፉ የተወሰዱትን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ማጠቃለያ የሚሰጥ ይሆናል።

የስነ ልቦናዊ ሂስ ምንነት
ስነ ልቦናዊ ሂስ በሲግመንድ ፍሩድ የስነ ልቦና መርሆዎች ላይ የተመሰረተ የሂስ አይነት ነዉ። የስነ ልቦና ንድፈ ሀሳብንና መርሆዎችንም መሰረት ያደርጋል። ይህ የስነ ጽሑፋዊ ሂስ የገጸ ባህሪያትን ዉስጣዊ ማንነት፣ ዝንባሌ፣ ፍላጎት እና ባህሪ ከስነ ልቦና አንፃር ይተነትናል። ገጸ ባህሪዉ ለሚያደርገዉ ድርጊት እና ለሚያስበዉ ሀሳብ መንስኤ የሚሆን ምክናያት አለ ብሎ ስለሚያምን ስነ ልቦናዊ ትንታኔ ያደርጋል። ማለትም ገጸ ባህሪያት ለሚያደርጉት ድርጊት እና ለሚያሳዩት የባህሪ ምስቅልቅልነት መንስኤዉ ምን እንደሆነ ያጠናል። ለምሳሌ አንድ ሰዉ በጎልማሳነቱ ለሚያሳየዉ ባህሪ በልጅነቱ ወቅት በቤተሰቡም ሆነ በአካባቢዉ ገጥሞት የነበረዉ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ገጠመኝ መሰረት ሊሆነዉ ይችላል። በሌላ በኩል የልጅነት የአስተዳደግ ሁኔታ በኋላኛዉ ዘመን ለሚያሳየዉ ባህሪ መሰረት ይሆነዋል ማለት ነዉ።

በስነ ልቦናዊ ሂስ ሀያስያን የሰዉ ልጅ ከጨቅላነት እስከ ሙሉ ሰዉነት ድረስ የሚመራባቸዉ የአዕምሮ ክፍሎች (ኢድ፣ ኢጎና ሱፐር ኢጎ) እንዲሁም ስነልቦናዊ ትወራዎች መሰረት በማድረግ የሂስ ስራቸዉን በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ላይ ያካሂዳሉ።በተጨማሪም የፍሩድን የህጻናት አስተዳደግ ስነ ልቦና (ኦራል፣ አናልና ጀኒታል) ደረጃዎችን የገጸ ባህሪያትን ማንነትና ባህሪ ለመገምገም ይጠቀሙባቸዋል። በዚህ አጭር ጽሁፍም የተለያዩ ስነ ልቦናዊ ንድፈ ሐሳቦችን ወይም መርሆዎችን መሰረት በማድረግ «ራህማቶ» የተሰኘዉን ረጅም ልቦለድ ለመገምገም ይሞከራል። የሚከተሉትን የስነልቦናዊ ሂስ ጥያቄዎች መሪ በማድረግም ስነ ልቦናዊ ሂስ ይደረጋል።
  1. የገጸ ባህሪዉ አስተዳደግ ሙሉ ሰዉ ሲሆን ተገልጧል?
  2. ከስነ ልቦናዊ ጽንሰ ሀሳቦች አንፃር የገጸ ባህሪያት ዉድቀት፣ ቀዉስ እና ፆታዊ ግንኙነት እንዴት ቀርቧል?
  3. በገጸ ባህሪዉ ድርጊትና ባህሪ ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና ያሳደረበት ተፅዕኖ አለ?

የልቦለዱ አጽመ ታሪክ
በአንድ ወቅት በደብረ ዘይት ከተማ የሚኖሩ ከማልና ዘርፌ የሚባሉ ባልና ሚስቶች ነበሩ። በቆይታቸዉ ሁለት ልጆችን ቢወልዱም በህይወት አልቆዩላቸዉም። ሶስተኛ ልጃቸዉ ራህማቶ ሲወለድ ደግሞ ዘርፌ ከዚህ አለም በሞት ተለየች። ራህማቶን አባቱ ከማል በጀርባዉ እያዘለ ጎረቤታቸዉ ወይዘሮ ፋጡማ ጡት እያጠቡ አሳደጉት። ከማል የሚሰራዉ በአንድ የመስታወትና የፍሬም መሸጫ መደብር በሀምሳ ብር ተቀጥሮ ነዉ። በዚህም የተነሳ ራህማቶ፥ የልጅነት ጊዜዉን እንደ አብዛኞቹ የሰፈሩ ልጆች ጭቃ አቡክቶ፣ ዉሀ ተራጭቶ እና ከዕኩዮቹ ጋር ተላፍቶ አላሳለፈም። ይልቁንም አባቱ በተቀጠረበት ቦታ ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ መላላክ ጀመረ። በመደብሩም የቅዱሳን አማልዕክት ምስሎች ልዩ ልዩ ስዕሎችና ፖስት ካርዶች በፍሬሞች እየተንቆጠቆጡ ለሽያጭ ይቀርባሉ። ራህማቶም በህጻን ልቦናዉ እነዚህ ስዕሎች በአዕምሮዉ ተቀረጹበት። ባገኘዉ ነገር ላይም የሚያያቸዉን ስዕሎች አስመስሎ ለመሳል ጥረት ያደርግ ጀመር። ከጊዜ ወደጊዜ እድሜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለስዕል ጥበብ ያለዉ ፍቅርም እየጠነከረ ሄደ። ምኞቱን ለማሳካትና የስዕል ጥበብ ፍቅሩን ለማርካት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘዉ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ተማሪ ለመሆን በቃ። ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ የተዋወቀዉ የቅርብ ጓደኛዉ ኬሎ ደግሞ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ተማሪ ነዉ።

ራህማቶ ለሁለት ዓመታት የስነ ጥበብ ትምህርት መማሩ ለስዕል ያለዉን ፍቅር አስታግሶለት ይሁን ሌላ ፍቅር ተጨምሮበት የስነ ጽሑፍ ፍቅር አደረብኝ በማለት ሥነ ጽሑፍ ለመማር ወሰነ። ዉሳኔዉንም አፀናዉ ተገበረዉም። ሁለት ዓመትም ሆነዉ። ጓደኛዉ ኬሎ ደግሞ ለመመረቅ አምስት ወራት ብቻ ቀርተዉታል። ራህማቶ ለስዕል ያለዉ ፍቅር እንደገና አገረሸበትና የስነ ጽሑፍ ትምህርቱን አቋርጦ የስዕል ስራ ለመስራት ወሰነ። ኬሎም ቢመክረዉ ቢመክረዉ አልመለስለት ስላለ የስዕል ስራዉን ለመጀመር የሚያስችሉትን ቁሳቁሶች ለዉድ ጓደኛዉ ለማሟላት ምኞት አደረበት።

ኬሎ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከፍተኛ ዉጤት በማምጣት ስላጠናቀቀ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆኖ የመቅረት ዕድል አጋጠመዉ። ለራህማቶም እንደተመኘዉ የስዕል ስራዉን የሚጀምርበትን ሁኔታ አመቻቸለት። ራህማቶ ስራዉን ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ስዕሎቹን ለኤግዚቢሽን አቀረበ። ለተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም ማከፋፈል ጀመረ። አድናቂና ገዥ ግን አልተገኘም። ይሁን እንጂ ራህማቶ ለስዕል ያለዉ ፍቅር አልቀነሰም። ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ደግሞ አንድ ማርታ የምትባል የ11ኛ ክፍል ተማሪ ያፈቅራል፡፡ ፍቅር የነበረዉ በሁለቱም ወገን በኩል ስለነበረ ሁለቱም ተስማሙ። ማርታ ትምህርቷን አቋርጣ ከቤተሰቦቿ ፈቃድ ዉጭ ከራህማቶ ጋር መኖር ጀመረች። ራህማቶም የስዕል ስራዉን ቀጠለ። ነገር ግን ገዥ ማግኘት ባለመቻሉ መሰረታዊ ፍላጎታቸዉን እንኳ ማሟላት አልቻሉም። ርዳታ የሚያደርግላቸዉ ኬሎ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኬሎ ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄደ። ራህማቶ በኪነ ጥበብ ፍቅርና በማርታ ፍቅር ተሰቃየ። ሁለቱን በአንድ ላይ ለማስኬድ ተቸገር። ሙያዉን ሲያፈቅር ማርታ ታኮርፋለች፤ ማርታን ሲያፈቅር ብሩሹ ታኮርፋለች። ይህ ሁኔታ ለራህማቶ ጥሩ አልሆነለትም።

ማርታ ራህማቶ ለስዕሉ የሚሰጠዉ ፍቅር ለእርሷ ከሚሰጣት ፍቅር እየበለጠ ታያት። አብረዉ ተኝተዉ ትቷት ስዕል ለመሳል ይነሳል። የምታደርገዉ አጣች። ይባስ ብሎ አንድ ቀን ሌሊት ሁለቱም በፍቅር ዉቅያኖስ ሰምጠዉ እየዋኙ እያሉ ራህማቶ ድንገት የስዕል ፍቅሩ ያይልበትና ከማርታ እቅፍ ተስፈንጥሮ ወጥቶ ሌሊቱን ስዕል በመሳል አነጋዉ። ማርታ ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዐይኗ ሳይዞርባት በንዴት ስትናጥ አደረች። ራህማቶ ሊነጋ ሲል መጥቶ ከአልጋዉ ላይ ጋደም ሲል እንቅልፍ ወሰደዉ። ማርታ ለራህማቶ ካላት ጽኑ ፍቅር የተነሳና ለስዕሎቹ እያለ እርሷን የዘነጋት ስለመሰላት ቡሩሹን ሰባበረች፤ በወረቀት ላይ የሳላቸዉን ስዕሎች ቀዳደደች፤ በጨርቅ የተሳሉትንም እንዲሁ አደረገች፤ በእንጨት ላይ የተሳሉትንም ሰባበረቻቸዉ። ራህማቶ ከዕንቅልፉ ሲነሳ የሆነዉን ሁሉ ለማመን ተቸገረ፡፡ እየቆየ ግን እዉነትነቱን እየተረዳ ሄደ። በዚህም የተነሳ በሁለቱ ፍቅረኛሞች መካከል ቅራኔ ተፈጠረ። ብዙም መጠጥ የማያዘወትረዉ ራህማቶ በሁኔታዉ የተነሳ እስከሚሰክር መጠጣት እምሽቶ መምጣት ጀመረ። ይባስ ብሎም ከአራት ቀን በሁላ በዚያዉ ማደር ጀመረ። ማርታ ይበልጥ ተናደደች። የምታፈቅረዉ ሰዉ ፍቅር እየሰጠችዉ እርሱ ፍቅር አለመስጠቱ የባሰ አንገበገባት።

ማርታ በሁኔታዎች ሁሉ አለመጣጣም የምታደርገዉ አጣች። ብዙ ካወጣች ካወረደች በኋላ ራሷን ለማጥፋት ወሰነች። ራሷንም እንደምታጠፋ ለራህማቶ ደብዳቤ ጽፋ በቀላሉ ሊመለከተዉ በሚችለዉ ቦታ ከአልጋዉ ላይ አስቀምጣለት ሄደች። በዕለቱ ራህማቶ ራሱን ስቶ በመጠጥ የዛለ ሰዉነቱን እየጎተተና እየተንገዳገደ በጊዜ ወደ ቤቱ መጣ። ማርታ በማለት በተደጋጋሚ ቢጣራም መልስ የሚሰጠዉ አላገኘም። እርሱም ለመልሱ ሳይጨነቅ ከመጠን በላይ ጠጥቶ ስለነበረ ከአልጋዉ ላይ ዧ ብሎ ወደቀ።  ስካሩ በመጠኑ በረድ ሲልለትና ሰዉነቱ መነቃቃት ሲጀምር ከመኝታዉ ተነስቶ ማርታን ፈለጋት። ግን ሊያገኛት አልቻለም። ቆም ብሎ አካባቢዉን ሲቃኝ የተጨማደደች ወረቀት ከአልጋዉ ላይ ተመለከተ። ወረቀቷን ካለችበት አንስቶ ማንበብ እንደጀመረ ከቤቱ ወጥቶ ወደ አራት ኪሎ በረረ። እየሮጠ እንዳለ ቆም ብሎ ሲመለከት ወረቀቱ ከእጁ የለም። ወደ ኋላ ወደ ፊት እየተመላለሰ ወረቀቱን ቢፈልገዉ ሊያገኘዉ አልቻለም። በዚች ዕለት ማርታንም ደብዳቤዋንም ተነጠቀ። ሁለቱንም ፍለጋ እንደወጣ ቀረ። ራህማቶም ከዚያች ቀን ጀምሮ በመላ አራት ኪሎ እብድ እንደሆነ ታወቀ። ህመሙም የሚነሳበት በምሽት ስለሆነ «ራሚ የምሽት ታማሚ» የሚል ቅፅል ስም ተሰጠዉ። ራህማቶ ቀን በሰላም ይዉላል ምሽት ያገኘዉን ወረቀት ሁሉ ይሰበስባል።

ይህ ሁሉ በሆነ አንድ ዓመት ከሁለት ወር በኋላ ኬሎ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። የራህማቶን ሁኔታ አወቀ። ከልቡም አዘነ። ዉድ ጓደኛዉን የተሰበረ ልቦናዉን ጠግኖ ቀድሞ ወደ ነበረበት ማንነቱ ለመመለስ ለራሱ ቃል ገባ። ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ራህማቶ ወደ ቀድሞዉ ሰባዊነቱ ለመመለስ በቃ። ማርታም ባልተጠበቀ ሁኔታ በህይወት ተገኘች።


«ራህማቶ» ከስነልቦናዊ ሂስ አንፃር
በዚህ ርዕስ ስር በገጽ አንድ ላይ የቀረቡትን የስነልቦናዊ ሂስ ንድፈ ሐሳቦች መሰረት በማድረግ የልቦለዱ ገጸ ባህሪያት ለሚያከናዉኑት ተግባርና ለሚያሳዩት ባህሪ ምን ስነ ልቦናዊ ምክናያት እንደሚኖር እያንዳንዱን ገጸ ባህሪ በዝርዝር ለመመልከት ሙከራ ተደርጓል።

የልቦለዱ ዋና ገጸ ባህሪ ራህማቶ የተለያዩ ባህሪያትን ሲያሳይና የተለያዩ ተግባራትን ሲፈፅም ይስተዋላል። ለምሳሌ ራህማቶ ከሚያሳየዉ ባህሪ መካከል ከፍተኛ የሆነ የስዕል ፍቅር አለበት። በገጽ አንድ ላይ ስለ ስነ ልቦናዊ ሂስ ምንነት ባነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ደግሞ ሰዎች በኋላ ላይ ለሚያሳዩት ባህሪ የልጅነት አስተዳደጋቸዉ እንደሚወስነዉ አንስተን ነበር። ራህማቶም ይህ የስዕል ጥበብ ፍቅሩ ያደረበት ያለ ምክናያት አይደለም። በልቦለዱ አጽመ ታሪክ ላይ እንደተገለጸዉ የራህማቶ አባት የሚሰራዉ በስዕልና በፖስት ካርድ መሸጫ መደብር በመሆኑና ራህማቶም እነዚያን ስዕሎች እየተመለከተ በማደጉ የተነሳ ነዉ። ራህማቶ ከአምስት ዓመቱ ገደማ ጀምሮ በዚሁ መደብር መላላክ ስለጀመረና የተለያዩ ስዕሎችንም ስለሚመለከት ከፍተኛ የሆነ አስመስሎ የመቅረጽ ፍላጎት አደረበት። ባገኘዉ ነገር ላይ ሁሉ የሚያያቸዉን ስዕሎች አስመስሎ ለመሳል ሙከራ ያደርግ ጀመር፡፡ ይህ የስዕል ጥበብ ፍቅሩ ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ ሙሉ ሰዉነቱ ድረስ አብሮት ዘለቀ። በፍሩድ የስነልቦና መርሆዎች መሰረትም የገጸ ባህሪዉ አስተዳደግ በገጸ ባህሪዉ ተግባር ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደቻለ ይሳያል።

ራህማቶ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ከጓደኞቹ ጋር ደብለቅ ብሎ ከመጫዎት ይልቅ ብቻዉን ገለል ብሎ በመቀመጥ በሀሳብ መዋተት ያዘወትር ነበር። ይህን የሚያደርገዉም እናቱ እሱን በወለደች ጊዜ እንደሞተች ስላወቀ በእኔ ምክናያት ህይወቷን አጣች እያለ ስለሚያስብና ያለ እናት ስላደገ ዉስጡን የደስተኝነት ስሜት ሊሰማዉ ስላልቻለ ነዉ። ይህም ገጸ ባህሪዉ ለሚያሳየዉ ባህሪ ምክናያት የሆነዉ ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ነዉ።

ራህማቶ የባህሪ ምስቅልቅልነትም ይታይበታል። በአንድ አላማ ላይ አይጸናም። ለዚህ ባህሪዉም ምክናያት አለዉ። ራህማቶ መጀመሪያ የስዕል ፍቅር አደረበት። ቀጥሎ የስነ ጽሑፍ ፍቅር ተጠናወተዉ። በመጨረሻም ከማርታ ጋር ፍቅር ጀመረ። ራህማቶ በአንድ በኩል በኪነ ጥበብ ፍቅር በሌላ በኩል ደግሞ በማርታ ፍቅር ይዋትታል። አንዱን ለመምረጥም ይቸገራል። የኪነ ጥበቡንም የማርታንም ፍቅር ጎን ለጎን ለማስኬድ ሞከረ አልተሳካለትም። ለዚህ የባህሪ ምስቅልቅልነቱም ምክናያት አለዉ። ይኸዉም ከላይ እንደተገለጸዉ ለጥበብ ያለዉ ፍቅር ከአስተዳደጉ ጋር በተያያዘ የመጣ ሲሆን ለማርታ ያለዉ ፍቅር ደግሞ በስነ ልቦና ምሁራን ዘንድ የሰዉ ልጅ የስነ ልቦናዊ አስተዳደግ ደረጃዎች ተብለዉ የሚታወቁት ነገሮች የፈጠሩት ተፅዕኖ ነዉ። ለምሳሌ በፍሩድ የህጻናት አስተዳደግ ስነ ልቦና መሰረት የህጻናት የዕድሜ ክልል በተለያየ ቁጥር የመደሰቻ አጋጣሚዎችም እየተለያዩ ይሔዳሉ። ህጻናት «ኦራል» ደረጃ ላይ ሲሆኑ የሚያስደስታቸዉ ቃላዊ የሆነ ነገር ሲሆን «አናል» በሚባለዉ ደረጃ ላይ ደግሞ ከመጸዳዳት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ይደሰታሉ። «ጀኒታል» ላይ ሲደርሱ ደግሞ የሚደሰቱት ከተቃራኒ ፆታ ጋር በሚኖራቸዉ ግንኙነት ነዉ። ስለሆነም ራህማቶ ከማርታ ጋር ፍቅር የጀመረዉ  በዚህ የሰዉ ልጆች አስተዳደግ ስነ ልቦና መሰረት የሚገኘዉ «ጀኒታል» ደረጃ ላይ በመሆኑ ነዉ። በእነዚህ በሁለቱ ፍቅር በመዉደቁ የተነሳ የባህሪ ምስቅልቅልነት ሊደርስበት ችሏል፡፡

ራህማቶ የማርታና የጥበብ ፍቅሩ ይጋጩበትና ሁለቱን ማስኬድ ከባድ ይሆንበታል። በሁኔታዉም የተነሳ ለዕብደት ይዳረጋል። ዕብድነቱም ተረጋግጦ «ራሚ የምሽት ታማሚ» ተብሎ በመላ አራት ኪሎ ታወቀ። ራህማቶ ህመሙ የሚነሳበት ምሽት ላይ ነዉ። ህመሙ በሚነሳበት ወቅት የሚተገብረዉ ተግባር ደግሞ የወዳደቁ ወረቀቶችን ሁሉ መልቀም ነዉ። ከስነ ልቦናዊ ሂስ አንፃር ራህማቶ ለሚተገብራቸዉ ተግባራት ሁሉ ምክናያት አለዉ። ይኸዉም ህመሙ ምሽት ላይ የሚነሳበት ማርታ ራሷን ልታጠፋ እንደሄደች ያወቀ በምሽት በመሆኑ ምሽት ላይ ቢፈልጋት የማገኛት  እየመሰለዉ ሲሆን፣ የወዳደቁ ወረቀቶችን የሚለቃቅም ደግሞ ማርታ ጽፋለት የሄደችዉን ደብዳቤ ሙሉ በሙሉ ሳያነበዉ ከዕጁ ስለጠፋዉ የማገኘዉ እየመሰለዉ ያገኘዉን ወረቀት ሁሉ ይሰበስባል።

ሌላኛዋ ገጸ ባህሪ ማርታ ከስነ ልቦናዊ ሂስ አንፃር ስትታይ የሰዉ ልጅ ከሚመራባቸዉ የአዕምሮ ክፍሎች መካከል የ«ኢድ»ን ተግባር በተደጋጋሚ ስትፈጽም ትስተዋላለች። እንደ ፍሩድ አተያይ «ኢድ» በምንም ተፅዕኖ ስር ሳንወድቅ ለምክናያት ሳንጨነቅ የሚያስደስተንን ነገር ሁሉ እንድንፈጽም የሚገፋፋን ክፍል ነዉ። ደመነፍሳዊ የሆነ ሀሴትንም የሚፈልግ ነዉ። ማርታም የምትተገብራቸዉ ተግባራት ምክናያታዊ ሳይሆኑ ከ«ኢድ» የመነጩና ደመ ነፍሳዊ ሀሴትን የሚፈልጉ ናቸዉ። ለምሳሌ ከቤተሰቦቿ ጠፍታ ወደ ራህማቶ ስትሄድ ለርሱ ያላትን ፍቅር ለማስታገስ ብቻ እንጂ ስለ ቤተሰቦቿ ያሰበችዉ ነገር የለም። ከራህማቶ ጋር በምትኖርበት ወቅትም የራሷን የዉስጥ ፍላጎት ብቻ በማዳመጥ በኋላ ለሚከሰተዉ ነገር ባለመጨነቅ የራህማቶን ብሩሽ ሰበረች። ስዕሎችንም አበላሸች። ይህን ሁሉ ያደረገችዉ ግን የሚትፈልገዉን የራህማቶን ፍቅር ለማግኘት ስትል ነዉ። ዳሩ ግን ይህ ተግባሯ ከራህማቶ ጋር የበለጠ አራራቃቸዉ እንጂ አላቀራረባቸዉም። ምናልባትም የ«ኢጎ» ጣልቃ ገብነት ቢኖር ኖሮ ማርታ ፍቅሯን ከማጣት ራህማቶም ከዕብደት ሊድኑ ይችሉ ነበር። ምክናያቱም «ኢጎ» ምክናያታዊ ነዉና ማርታ ይህን ብፈጽም ይህ ይከሰትብኛል የሚል ምክናያታዊ የሆነ ጥያቄ አዕምሮዋ ሊያመነጭ ይችል ነበር። ሆኖም የ«ኢድ» ፍላጎት አየለና ለሁለታቸዉ መለያየት ምክናያት ሊሆን ቻለ።

ማርታ ራሷን ለማጥፋት ያሰበችም ያለምክናያት አይደለም። ራህማቶ በኪነ ጥበብ ፍቅር ተተብትቦ እርሷን የተዋትና የጠላት ስለመሰላት ነዉ። በተጨማሪም ራህማቶ ቢተዋት ቀደም ከቤተሰቦቿ ፈቃድ ወጥታ ስለመጣች የምትጠጋበት እንደሌላት እየታወሳትና አባቷ መሞታቸዉን በመስማቷ በዉስጧ የተሰነቀረዉ ሀዘን አላስችል ብሏት ነዉ። ይህን ሁሉ ስታስበዉ የወደፊት ህይወቷ ጨለማ መስሎ ስለታያት ራሷን ለማጥፋት ወሰነች።

ማጠቃለያ
በዚህ ጽሑፍ በ «ራህማቶ» ረጅም ልቦለድ ዉስጥ ያሉ ገጸ ባህሪያት ስነ ልቦና ምን እንደሚመስል ለማየት ተችሏል። በተለይ ሁለቱ ገጸ ባህሪያት የሚያሳዩትን ባህሪና የሚፈጽሙትን ድርጊት ከተለያዩ የስነ ልቦናዊ ሂስ ንድፈ ሐሳቦች አንፃር ለመመልከት ተችሏል። ለምሳሌ ዋናዉ ገጸ ባህሪ ራህማቶ ከፍተኛ የሆነ የኪነ ጥበብ ፍቅር አለበት። ደስተኛነት ብዙም አይሰማዉም። የባህሪ ምስቅልቅልነትም ይታይበታል። በተጨማሪም በአዕምሮዉ ዉስጥ ስነ ልቦናዊ ግጭት ይስተዋልበታል። ለእነዚህ ባህሪያቱና ድርጊቱ ደግሞ ስነ ልቦናዊ የሆነ ምክናያት አለዉ። ለስዕል ያለዉ ፍቅርና ደስተኛ አለመሆኑ አስተዳደጉ ከፈጠረበት ተፅዕኖ የመነጨ ሲሆን የሚያሳየዉ የባህሪ ምስቅልቅልነት ደግሞ በዉስጡ ካለዉ የፍላጎት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ የመጣ ነዉ።

ማርታንም ከስነልቦናዊ ሂስ አንፃር ስንመለከታት የሚያስደስታትን ነገር ሁሉ ከመተግበር ወደ ኋላ አትልም። ይኸዉም «ኢድ» ከሌሎች የአዕምሮ ክፍሎች ከፍተኛ ድርሻ በመዉሰዱ ነዉ። ለዚህም ነዉ ማርታ የራህማቶን ቡሩሽ የሰበረችና ስዕሎቹን ያበላሸች።

በአጠቃላይ በተደረገዉ የስነ ልቦናዊ ሂስ ስራ በልቦለዱ ዉስጥ ያሉት ገጸ ባህሪያት ለሚያሳዩት ባህሪና ለሚተገብሩት ተግባር የአስተዳደግ ሁኔታቸዉና የተለያዩ ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ምክናያት እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም የገጸ ባህሪያት ፆታዊ ግንኙነት ከሰዉ ልጅ የአስተዳደግ ስነ ልቦና ንድፈ ሐሳቦች አንፃር ምን እንደሚመስል ታይቷል።

2015 ማርች 27, ዓርብ

ረጅም ልቦለድ

የረጅም ልቦለድ መከፋፈያ መስፈርቶች
ለረጅም ልቦለድ አይነቶች ወጥ የሆነ የመከፋፈያ መስፈርት አለ ለማለት ቢያስቸግርም አብዛኛዉን ጊዜ ረጅም ልቦለድን ለመከፋፈል ይዘትን ወይም ጭብጥንና በልቦለዱ ዉስጥ የሚቀርቡ ክንዋኔዎችን መሰረት በማድረግ መከፋፈል የተለመደ ተግባር ነዉ። ከዚህም በተጨማሪ የተቀረጹ መቼቶችና ገጸባህሪያት ለልቦለድ መከፋፈያ መስፈርት በመሆን ያገለግላሉ።
ይዘትን ወይም ጭብጥን መሰረት በማድረግ ፖለቲካዊ፣ ስነ ምግባራዊ፣ ስነ ሰባዊ ወዘተ በማለት መከፋፈል ይቻላል። ፖለቲካዊ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያካትተዉን ፖለቲካዊ፣ ስለ ስነምግባር የሚሰብከዉን ስነ ምግባራዊ፣ የማህበረሰቡን ባህላዊና ማህበራዊ እዉነታዎች የሚያንጸባርቀዉን ስነ ሰባዊ ልቦለድ በማለት መፈረጅ ወይም መመደብ ይቻላል።

የሚቀረጹ ገጸባህሪያትን መሰረት በማድረግ ደግሞ አሊጎሪያዊ፣ ታሪካዊ፣ ደብዳቤያዊ ወዘተ በማለት መከፋፈል ይቻላል። የተቀረጹት ገጸባህሪያት እንስሳትና ረቂቅ ነገሮች ወይም ግኡዛን አካላት ከሆኑ አሊጎሪያዊ፣ ታዋቂ ባለታሪኮች ገጸባህሪ፥ ታሪካዊ ቦታወች መቼቶች ሆነዉ የሚቀርቡበትን ደግሞ ታሪካዊ ልቦለድ በማለት መመደብ ይቻላል።

ይሁን እንጂ ከላይ የቀረቡት የመከፋፈያ መስፈርቶች ወጥነት ያላቸዉ ናቸዉ ለማለት አያስደፍርም። ይኸዉም በአንዱ ልቦለድ ዉስጥ የተገለጹ ጉዳዮች በሌላዉ ዉስጥ ሊገኙ የሚችሉ መሆናቸዉ ነዉ። ለምሳሌ በአሊጎሪያዊ ልቦለድ በገጸባህሪያት አማካኝነት ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ሊተቹ፣ ሊገመገሙና ሊፈተሹ፣ ስነ ምግባር ሊሰበክና አጠቃላይ ስነ ሰባዊ ጉዳዮች ሊገለጹ ይችላሉ። ይህ የአንዱ ልቦለድ ይዘት በሌላዉ ዉስጥ ተካቶ መገኘት የመከፋፈያ መስፈርቱን የተጣራ አለመሆን ያሳያል። ከዚህ በመነሳትም የመከፋፈያ መስፈርቱ ክፍተት ያለበት ነዉ ለማለት ይቻላል። ይሁንና የተለያዩ ጥናቶች ተጠንተዉ የተጣራ መክፈያ እስከሚገኝ በዚህ መስፈርት መጠቀም ይቻላል።

የረጅም ልቦለድ አይነቶች
የልቦለድ መከፋፈያ መስፈርቶች እነዚህ ናቸዉ ብሎ በርግጠኝነት መናገር እንደሚያስቸግር ሁሉ የልቦለድ አይነቶችንም ይህን ያህል ናችዉ ብሎ ለመወሰን ያዳግታል። በርካታ የረጅም ልቦለድ አይነቶች እንዳሉ ብርሐኑ (2009፣ 32) ይገልጻሉ።

ከላይ በቀረበዉ የረጅም ልቦለድ መከፋፈያ መስፈርት መሰረትም የተለያዩ የረጅም ልቦለድ አይነቶች አሉ። እነሱም ፖለቲካዊ፣ ስነ ሰባዊ፣ ስነ ምግባራዊ፣ ደብዳቤያዊ፣ ታሪካዊ፣ አሊጎሪያዊ፣ ምጸታዊ ወዘተ ናቸዉ። ይሁንና የኛ የትኩረት አቅጣጫ ሶስቱን የልቦለድ አይነቶች ማብራራት ወይም መግለጽ በመሆኑ እንደሚከተለዉ ለመግለጽ ተሞክሯል።

ስነ ምግባራዊ ልቦለድ
ይህ የልቦለድ አይነት ከህብረተሰቡ እዉነታ ጋር የተቀራረበ ነዉ። ማለትም በታሪኩ ዉስጥ የሚጠቀሱ ቦታዎችና ስሞች ታሪኩ ከተቀረጸበት ማህበረሰብ ባህል ወግና ልማድ ጋር የተቀራረቡ ናቸዉ። ስነ ሰባዊ ልቦለድ የተቀረጸበትን መቼት (ጊዜና ቦታ) ከማህበረሰቡ ወግና ልማድ ጋር አዋህዶና እዉነታዊነትን አላብሶ የማቅረብ አቅም አለዉ። ይህ ልቦለድ ሰወች በተወሰነ ቦታና ጊዜ የፈጸሟቸዉን፣ ወደፊት የሚፈጽሟቸዉንና እየፈጸሟቸዉ ያሉትን ድርጊቶች ከማህበረሰቡ እዉነታ ጋር በማቀራረብ በገጸባህሪያት አማካኝነት ይገልጻል።
ፖለቲካዊ ልቦለድ
ይህ የልቦለድ አይነት በመተግበር ላይ ያሉ ፖሊሲዎችን፣ የፖለቲካ ሰዎችን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድሪጅቶችን፣የአስተዳደር አካላትን ወዘተ በገጸባህሪያት አማካኝነት በመሳል ስላለዉ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚገልጽ የልቦለድ አይነት ነዉ። ይህ የልቦለድ አይነት ያለፈዉ ፖለቲካዊ ስርአት ምን እንደነበር፣ የዛሬዉ ምን እንደሚመስል አዝናኝና እዉናዊ በሆነ መልኩ ይተችበታል።

ፖለቲካዊ ልቦለድ የደራሲዉ የግል ስሜት የሚንጸባረቅበት ሳይሆን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉን ሀሳቦች የሚያቀርብ፣ በቀጥታ ስለ ፖለቲካዊ ክስተቶች የሚገልጽ፣ የሚተረጉምና የሚተነትን ዝርዉ የፈጠራ ስራ ነዉ ሲሉ ሞሪስ ጆሴፍን ጠቅሰዉ ይገልጻሉ።

በፖለቲካዊ ልቦለድ ዉስጥ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉ ሀሳቦች ወሳኝነት አላቸዉ። መቼቱም አንድ ፖለቲካ የነበረበት ጊዜና ቦታዎች ናቸዉ ሲሉ ኤርቪንግ ይገልጻሉ።

ከእነዚህ ሁለት ምሁራን ሃሳብ የምንረዳዉ ፖለቲካዊ ልቦለድ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉን ሃሳቦች የሚገልጽ የደራሲዉ የምናብ ዉጤት መሆኑን ነዉ።

ስነ ምግባራዊ ሂስ

የስነ ምግባራዊ ሂስ ትንተና
መግቢያ
ስነ ምግባራዊ ሂስ በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ ባህላዊና ሀይማኖታዊ የስነምግባር መርሆዎችን መሰረት በማድረግ በአንድ የስነ ጽሑፍ ስራ ላይ የሚደረግ ምዘና ነዉ። በዚህ ሂስ ሀያሲዉ የቀረበዉ ስነ ጽሁፍ ምን ያህል ስነ ምግባርን ሊያስተምር እንደሚችል ይፈትሻል።  በዚህ አጭር ጽሁፍም ስነ ምግባራዊ ሂስ ምን እንደሚመስል እርቂሁን በላይነህ በ2000 ዓ.ም ያልተጠቡ ጡቶችና ሌሎችም በሚለዉ የአጭር ልቦለድ መድብል ዉስጥ በካራን የተገኘ መሲህ በሚል ርዕስ ያቀረበዉን ልቦለድ በተግባር ለመፈተሽ ሙከራ ይደረጋል።

የልቦለዱ አጽመ ታሪክ
አንድ ማርታ የምትባል ልጅ በካራን ትኖር ነበር። ማርታ አባቷ በህፃንነቷ ስለሞተባት እናትም አባትም ሆና ያሳደገቻት እናቷ ናት። የማርታ እናት ማርታን አሳድጋ አስተምራ  በአንድ መስሪያ ቤት በጸሀፊነት ተቀጥራ እያለች ታመመች። ማርታም ለእናቷ ማሳከሚያ የሚሆን 20 ሺህ ብር ተጠየቀች። ይህን የህክምና ወጭ ከፍላ የእናቷን ህይወት ከሞት ለመታደግ ያላደረገችዉ የለም። እናቷን ለማስታመም ከስራ ስለምትቀር ከስራዋ ተባረረች፤ ገንዘብ አገኝበታለሁ ብላ ያመነችበትን ተግባር ሁሉ መፈጸም ጀመረች። አስርቱ ትዕዛዛትን ተላለፈች። በሴተኛ አዳሪነት በመሰማራት የእናቷን ህይወት ለማትረፍ ስትል አታመንዝር የሚለዉን ህግ ተላለፈች። በወንዶች ዘንድ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ስትል ድንግልና አለኝ በማለት መዋሸት ጀመረች። አይኗን ጭቃ በመቀባትና በመሸፈን ማየት የተሳነኝ በማለት መለመን ጀመረች። ገንዘብ ይኖረዋል ብላ ያሰበችዉን ሰዉ ለመዝረፍ ስትል ነፍስ አጠፋች። በመጨረሻም ይህን ሁሉ አድርጋ ሳይሳካላት ቢቀር ፈጣሪዋን በመካድና በፈጣሪዋ ተስፋ በመቁረጥ ወደ ደብተራ (ጠንቋይ) ዘንድ በመሔድ አጋንንት አስጎተተች መጽሐፍ አስገለጠች።

ማርታ ይህን ሁሉ አድርጋ እናቷን ከህመም መፈወስ አልቻለችም። በዚህ ሁኔታ አዝና ተክዛ እንደተቀመጠች ድንገት አማላክ በዐይነ ስጋ ተገልጦ አታቀርቅሪ ይላታል። ማርታ ግን አምላክነቱን አልተቀበለችም። ምክናያቱም አምላኳን ደጋግማ ለምና እናቷ ከህመሟ መፈወስ አልቻለችምና ነዉ። እኔ አምላክ ነኝ ሲላት አይደለህም ትለዋለች፤ ትሰድበዋለች፤ ታንጓጥጠዋለች፤ ትሳለቅበታለች። አምላክ አይደለህም አንተን የሩቁን ጩኸታችንን የማትሰማንን አምላክ ከምናመልክ ይልቅ የቅርቡን የምንዳስሰዉን የምንጨብጠዉን ደንጋዩን ብናመልክ የተሻለ ነዉ በማለት ትጮህበታለች። ከዚያም አምላኳን ትታ ደብተራዉ በነገራት መሰረት እናቷን መድሀኒት ስታጥናት አንድ ጊዜ ድምጽ አሰምታ ፀጥ ትልባታለች። መሲሁንም አንተ ቀናተኛ አምላክ አጋንንት አስጎትቼ መጽሐፍ አስገልጬ አንደበቷን ባስከፍተዉ መልሰህ ዘጋኸዉ በማለት ለፈለፈችበት። መሲሁም አሰርቱ ትዕዛዛቴን አላከበራችሁልኝም፤ በእጄ የፈጠርኳችሁ ፍጡሮቼ አምፃችሁብኛል፤ እያለ ማርታም አምላክ አይደለህም እያለች ስትሳለቅበት ከቆየች በኋላ አምላክ ከሆንክና ስልጣን ካለህ ስልጣንክን በተግባር አሳየኝ ከዚያም አምንሀለሁ አመልክሀለሁ አመሰግንሀለሁ ትለዋለች። ወዲያዉኑ መሲሁ እንግዲያዉስ የልብሽ ይሙላ በማለት ለዓመታት በህመም ስትሰቃይ የኖረችዉን የማርታን እናት ከህመም ፈወሰ፤ ማርታም አምላክነቱን በሚገባ አረጋገጠች፤ ማምስገንም ጀመረች።

በካራን የተገኘዉ መሲህ ከስነ ምግባራዊ ሂስ አንፃር
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በርካታ ሀይማኖታዊ መርሆዎች አሉ። ለምሳሌ አስርቱ ትዕዛዛት ተብለዉ ከሚታወቁት መካከል፦ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ አትግደል፣ ከአምላክህ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ የሚሉት ይገኙበታል። የዕምነቱ ተከታዮችም እነዚህን ሀይማኖታዊ ህግጋት ለመፈፀም ይጥራሉ። በዕርቅ ይሁን በላይነህ በ2002 ዓ.ም በተጸፈዉ ያልተጠቡ ጡቶች በሚለዉ የአጭር ልቦለድ መድብል ዉስጥ ካሉት ልቦለዶች መካከል በካራን የተገኘዉ መሲህ በሚለዉ አጭር ልቦለድ ዉስጥ በርካታ ሀይማኖታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጉዳዮች ተንፀባርቀዋል። የልቦለዱ ዋና ገጸባህሪ ማርታ በልቦለዱ ታሪክ ዉስጥ በተደጋጋሚ የእምነቱ ተከታዮች አጠንክረዉ የሚጠብቋቸዉንና የሚያከብሯቸዉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዛት ስትተላለፍ ትስተዋላለች።ሆኖም ግን ደራሲዉ ከስነምግባር አንፃር ማስተላለፍ የፈለገዉ አንባቢዎች ለእናት ያላቸዉ ፍቅር እንዲጨምርና ሀይማኖታቸዉ በሚያዝዘዉ መልኩ ስነምግባራቸዉን ማነጽ እንደሚገባቸዉ ነዉ፡፡
ገጸ ባህሪዋ በርካታ ስነምግባር የጎደለዉ ድርጊት ስትፈጽም ትታያለች። ሆኖም ግን ይህ አይነት ስነ ምግባር የትም ሊያደርስ እንደማይችል በታሪኩ መጨረሻ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። መዋሸት፣ አመንዝራነት፣ መግደል፣ በዛር በጠንቋይ ማምለክ ለዉርደት ለዉድቀት የሚዳርግ እንጂ የትም ሊያደርስ እንደማይችል ተገልጿል። ከታሪኩ ላይ እንደምንረዳዉ ማርታ የእናቷን ህመም በህክምና ለመከታተል ስትል በርካታ ትዕዛዛትን ተላልፋለች። ሆኖም በአንዱም ሲሳካላት አትስተዋልም። ዋሽታም፣ አመንዝራም፣ ነፍስ አጥፍታም ብር ልታገኝ አልቻለችም። የእናቷን ህመምም ማስታገስ አልቻለችም። በመጠኑም ቢሆን ትንሽ የተስፋ ጭላንጭልን ያሳያት የደብተራዉ ሙከራም ለደቂቃ የማይቆይ ተስፋ ሆነባት። ሙከራዋ ሁሉ ባዶ ሆነ። ደራሲዉ ገጸባህሪዋን በዚህ መልኩ ያቀረባትም ሆን ብሎ ይህ አይነት ስነምግባር የትም ሊያደርስ እንደማይችል ለአንባቢያን ለማስወቅ ካለዉ ፍላጎት የተነሳ  ነዉ። የአምላክን ትዕዛዝ ረስቶ ለአዋይ ለጠንቋይ ተገዝቶ እንኳንስ ከህመም መፈወስ አንድ ስንዝር እንኳ መራመድ የማይቻል መሆኑን ታሪኩ ይስገነዝባል። ልቦለዱም ይህ አይነት ስነ ምግባር ማለትም አምላክን የመካድ፣ ትዕዛዛትን ያለመፈፀም ወዘተ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዳይከሰት ለማስገንዘብ ያለዉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነዉ።

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በካራን የተገኘዉ መሲህ ከስነ ምግባራዊ ሂስ አንፃር ሲታይ አንባቢዎችን ጥሩ ስነምግባር ሊያስተምር የሚችል ነዉ። ከማህበረሰቡ ባህላዊ የስነምግባር መርህ አንፃር ሲታይ ዋናዋ ገጸ ባህሪ ለእናቷ የምታደርገዉ በጎ ስራና የምትከፍለዉ መስዋትነት በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉና ሊበረታታ የሚገባዉ ስነምግባር ነዉ። ከሀይማኖት አንፃር ደግሞ ሁሉም ነገር ያለ አምላክ ፈቃድ ሊሆን እንደማይችል ያሳያል። ስለሆነም በአምላክ ማመን እንደሚገባ ያስተምራል።

2015 ማርች 26, ሐሙስ

ድራማ

ድራማ
ድራማ የሚለዉ ቃል የእንግሊዘኛ ቃል ሲሆን ተዉኔት የሚለዉን  የአማርኛ ቃል እንዲወክል ተደርጎ የተሰየመ ቃል ነዉ። ተዉኔት በግጥም ወይም በተዋንያን ድርጊትና ምልልስ ታጅቦ በመድረክ ላይ የሚተወን ድርሰት ነዉ። አንዳንድ ሰዎች ድራማን ትያትር፣ ቤተ ተዉኔት፣ መራሂ ተዉኔት እያሉ ሲጠሩት ይስተዋላል። ነገር ግን እነዚህ ከድራማ ጋር ግንኙነት ያላቸዉ እንጂ ድራማን የሚወክሉ አይደሉም። ለምሳሌ ድራማ የሚቀርብበትን ስፍራ፣ የድራማዉን ድርሰት፣ የድራማዉን ሙያ፣ በመድረክ ላይ ያለዉን የአቀራረብ  ስልት የሚያጠቃልለዉ ቲያትር ሲባል የድራማዉ ደራሲ ወይም ጸሐፊ ደግሞ ጸሐፊ ተዉኔት ይባላል። ጸሐፊ ተዉኔቱ የፃፈዉን ድራማ አዘጋጅቶ ለመድረክ የሚያበቃዉ ደግሞ መራሒ ተዉኔት ይባላል።

ድራማ የተዋንያንን ንግግርና አካላዊ ተሳትፎ አጣምሮ በመድረክ ላይ የሚያቀርብ የሥነ ጽሑፍ  ዘርፍ ነዉ፡፡  የሰዉ ልጅ ስሜት፣ ፍላጎት፣ ፀባይ ገፀባህሪያትን በሚወክሉ ተዋንያን አማካኝነት በመድረክ ላይ የሚተወን ጥበብ ሲሆን ይህም ጥበብ በግጥም ወይም በዝርዉ ሊቀርብ ይችላል።

የድራማ ጥንተ አመጣጥ
ድራማ መቼ እና የት ተጀመረ ለሚለዉ ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ ማግኘት አይቻልም። ምክናያቱም የድራማ ቀለምና አሻራ ያላቸዉ የሥነ ጽሑፍ ዘርፎች በርካታ ከመሆናቸዉ የተነሳ ነዉ። ነገር ግን መደበኛ መልክ አስይዞ ድራማን ለተደራስያን በማቅረብ ረገድ ግሪኮችን ቀድሞ የተገኘ የለም። በዚች ሀገር ድራማ ከ2200  ዘመናት በፊት ከጥንታዊዉ የግሪክ ንጉስ  አዳዮናይሲስ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነዉ።

ከግሪኮች በመቀጠል በድራማ ታሪክ ስማቸዉ የሚጠራዉ ሮማዉያን ናቸዉ። ሮማዉያኖች በጥንታዊ የሀይማኖት ክብረ በዓላት በሞተ ጀግና መቃብር ላይ በህብረት የሚዘመሩ መንፈሳዊ መዝሙሮች እና በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ በክዋኔ የሚተረቱ ተረቶች ለድራማ ባህልና ጅማሮ መስፋፋት ምክናያቶች ናቸዉ። ለምሳሌ፦ በግብፅ የንጉስ ፈርዖን መዋዕለ ንግስና፣ በእንግሊዝ የሼክስፒር ስራዎች ተጠቃሽ ናቸዉ።

የድራማ አነሳስና እድገት በኢትዮጵያ
ለኢትዮጵያ ድራማ አነሳስና እድገት የላቀ አስተዋጽኦና ድርሻ አላቸዉ ብሎ ታሪክ የሚዘክራቸዉ ተክለሀዋርያት ተክለ ምርያም፣ ዮፍታሔ ንጉሴ፣ ከበደ ሚካኤል፣ መንግስቱ ለማ፣ ፀጋየ ገብረ መድህን፣ ተስፋየ ገሰሰና ደበበ ሰይፉ ናቸዉ። እነዚህ ደራሲያን በስራቸዉ ያነሷቸዉ ርዕሰ ጉዳዮችም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ የቀድሞዉንና የዘመኑን የባህል ግጭት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት፣  ግብረገብነት፣ የፍትህ እጦት እና አድሎ ናቸዉ።

ተክለሀዋርያት ተክለማርያም
በአማርኛ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የመጀመሪያዉ ፀሀፊ ተዉኔት ተክለሀዋርያት ተክለማርያም ናቸዉ። እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ድራማ የሆነዉን የአዉሬዎች መሳለቂያ ወይም ፋቡላ የተሰኘዉን ተዉኔት ደረሱ። በተዉኔቱም የዘመኑን የስልጣን ብልግና፣ ኋላቀርነትና ደካማ አስተዳደር ይፋ አዉጥተዉ አሳይተዋል። ጽሑፈ ተዉኔቱም በግጥም መልክ የቀረበ ነበር።

ዮፍታሔ ንጉሴ
እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት የመጀመሪያዉን ድራማ በ1923 ዓ.ም ጥቅም ያለበት ጨዋታ በሚል ርዕስ ደርሰዋል። የድራማዉ ይዘትም ሀይማኖታዊ ነበር። በዚሁ አመት ምስክር የሚል ሌላ ድራማም ደርሰዋል። በ1924 የሆድ አምላኩ ቅጣት እና ያማረ ምላሽ፣ በ1925 ዳዴ ተራ፣ በ1926 ሙሽሪት ሙሽራ፣ የህዝብ ፀፀት፣ ደግን ለመከተልና ክፉን ለመተዉ እንዲሁም ስለ ስጋ ደዌ በሽተኞች አንድ  ዝነኛ ድራማ ደርሰዋል። ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በፊት በ1927 መሼ በከንቱ፣ ጠረፍ ይጠበቅ፣ የደንቆሮዎች ቲያትር የተባሉ ድራማዎችን ደርሰዋል። በኢጣሊያን ወረራ ወቅትም አፍጀሽን የተሰኘዉን ድራማ ደርሰዋል። ይህ ስራቸዉ ድራማ የመፃፍ ችሎታቸዉን ያሳዩበት ድራማ ነበር። ዮፍታሔ በወቅቱ ድራማ ለመፃፍ ያነሳሳቸዉ አስተማሪ ስለነበሩ የድራማን ጥበብ በተግባር ለማሳየትና ድራማ ይመለከቱ ስለነበር እንዴት መቅረብ እንዳለበት ለማሳየት ካላቸዉ ፍላጎት የተነሳ እንደነበር ይነገራል።

በአጠቃላይ ዮፍታሔ ንጉሴ እስከ 1928 ዓ.ም በጠቅላላዉ 16 ድራማዎችን ደርሰዋል። ድራማዎችም በየመድረኩ በተደጋጋሚ ታይተዋል። የዚህ ዘመን ድራማ አባት በመባልም ይታወቃሉ። በ1939 እያዩ ማዘን የተሰኘዉን ባለ 5 ክፍል ድራማ ጽፈዋል። ይህ ድራማም በፀሀፊ ተዉኔቱ መራሔ ተዉኔትነት ተዘጋጅቶ በመድረክ ቀርቧል።

ከበደ ሚካኤል
እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት በግጥም ወይም በቅኔ ጥበብ የተቀኙና ወደ ድራማዉ አለምም ያዘነበሉ ነበሩ። በዚህ ረገድም አኒባል፣ ካሌብ፣ የትንቢት ቀጠሮ (ችሎታቸዉን ያሳዩበት) እና የቅጣት ማዕበል የተሰኙ ድራማዎችን ጽፈዉ ለመድረክ አበርክተዋል። የሼክስፒርን ሮሚዮና ጁሌትን እና የበርታ ክሌንን ከይቅርታ በላይ የተሰኙ ድራማዎች ወደ አማርኛ መልሰዋል።

መንግስቱ ለማ
እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት በአዲስ የድራማ አቀራረባቸዉ የሚታወቁ ሲሆኑ ኮሚዲ የተባለዉን የድራማ ዘዉግ ለኢትዮጵያ አስተዋዉቀዋል። በርከት ያሉ ድራማዎችንም ለኢትዮጵያ አበርክተዋል። ከነዚህም መካከል፦ ጠልፎ በኪሴ (ኮሚዲ የተዉኔት ዘዉግን ያሳዩበት)፣ ያላቻ ጋብቻ፣ በ1968 ባለካባና ባለዳባ፣ በ1969 ዘ ኢንስፔክተር የሚለዉን ድራማ ጠያቂዉ በሚል ርዕስ ተርጉመዋል። በ1974 ፀረ ኮለኒያሊስት፣ በ1978 ሹምያ እና የአንቶኒቸኮቬ ዘ ብሔር የተሰኘዉን ዳንዴዉ ጨቡዴ፣ የተዉፊክ አል ሀኪምን ላስት ቱ ኪል የተሰኘዉን ግደይ ግደይ አለኝ በሚል ባለ አንድ ገቢር ትይንቶች ተርጉመዋል። በድህረ አብዮትም  ባለ አንድ ገቢር የሆነዉን የዐለሙ ንጉስ የተሰኘዉን ድራማ ፅፈዋል።

ነጋሽ ገብረማር ያም
ይህ ጸሀፊ ተዉኔት በስራዎቹ ፖለቲካን ፊት ለፊት ይጋፈጥ ስለነበር አብዛኛዎቹ ስራዎች ተቃጥለዋል። ከተገኙት ተዉኔቶች መካከል የድል አጥቢያ አርበኛ እና የአዛዉንቶች ክበብ ተጠቃሽ ሲሆኑ ይዘታቸዉን ግን ለማወቅ እንዳልተቻለ ምሁራን ያስረዳሉ።

ፀጋየ ገብረ መድህን
በ1950ዎቹ ከከሸፈዉ መፈንቅለ መንግስት ጋር ተያይዞ የተነሳዉን የለዉጥ ሐሳብና በትዉልዶች መካከል በተከሰቱ የአስተሳሰብ ልዩነቶች የተነሳ ይንፀባረቅ የነበረዉን የባህል ግጭት በድራማዎቻቸዉ ያነሱ ነበር። ትራጀዲ የተሰኘዉን አዲስ የድራማ ዘዉግም አበርክተዋል። የፀጋየ የድራማ ስራዎች በከፊል በልግ፣ የከርሞ ሰዉ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ መልዕክተ ወዝ አደር፣ ሰቆቀዉ ጴጥሮስ፣ ሀሁ ወይም ፐፑ፣ እናት ዐለም ጠኑ፣ የራሱ ጽሑፈ ተዉኔቶች ሲሆኑ ከሼክስፒር የተተረጎሙ ስራዎች ደግሞ ኦቴሎ፣ ሀምሌትና ማክቤዝ ናቸዉ። ከፈረንሳዩ ፀሀፊ ተዉኔት ሞሊቬር የተተረጎመዉ ደግሞ ሙዚቀኛዉ ጆሮ ይገኙበታል። ቴዎድሮስ የተሰኘዉን የእንግሊዘኛ ድራማም ወደ አማርኛ ተርጉሟል።
 ተስፋየ ገሰሰ
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት በአሜሪካን አገር እያለ በ1953 ዓ.ም በእንግሊዘኛ ላቀችና ማሰሮዋ በሚል ጽፏል። በ1954 የሺን፣ በ1958 አባትና ልጆች፣ በ1961 ዕቃዉ የተሰኙ ድራማዎችን ጽፏል። እቃዉ የሚለዉ ድራማ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመድረክ ለመታየት የበቃ ነዉ። የዚህ ድራማ ርዕሰ ጉዳይም የሰዉ ልጅ ሲጨቆን፣ ሲንገላታና ሲሰቃይ ከዚህም አልፎ እንደ ዕቃ ተቆጥሮ ሰብአዊ ክብሩን ሙሉ በሙሉ ሲያጣ ይታያል። ድራማዉ ይህንን አይነት ድርጊት ያወግዛል።

ደራሲዉ ከነዚህም በተጨማሪ በ1966 ማነዉ ኢትዮጵያዊ፣ በ1970 ፍርዱን ለዕናንተዉ፣ በ1972 ተሀድሶ፣ በ1979 ሰኔና ሰኞ የተሰኙ ድራማዎችን ለመድረክ አብቅተዋል። ተስፋየ ጸሐፊ ተዉኔት ብቻ ሳይሆኑ መራሒ ተዉኔትም ተዋናይም ነበሩ።

ደበበ ሰይፉ
እኒህ ጸሐፊ ተዉኔት ከባህር የወጣ ዓሳ፣ ሳይቋጠር ሲተረተር፣ እነሱ እሷ፣ እናትና ልጆቹ የሚሉ ድራማዎችን ደርሰዋል፤ መራሒ ተዉኔትም ተዋናይም ነበሩ።

ብርሀኑ ዘሪሁን
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት በ1972 መረሸን፣ በ1975 ጣጠኛዉ ተዋናይ፣ በ1972 ባልቻ አባነፍሶን ደርሰዋል።

ስንዱ ገብሩ
እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት የመጀመሪያዋ ሴት ፀሀፊ ተዉኔት ሲሆኑ በ1938 ኮከብህ ያዉና ያበራል ገና የሚለዉን ተዉኔት የመጀመሪያ ስራቸዉ አድርገዉ አቅርበዋል።  በ1939 የየካቲት ቀኖች (ደራሲዋ የምትታወቅበት) የሚል ድራማ የደረሱ ሲሆን ይዘቱም የየካቲት 12ቱን ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ የሚዘክር ነበር። በ1940 የታደለች ህልም፣ ርዕስ የሌለዉ ትዳር፣ የኑሮ ስህተት፣ በ1943 ከማይጨዉ መልስ፣ ፊታዉራሪ ረታ አዳሙ የተሰኙ ተዉኔቶችን ደርሰዋል። ያበረከቷቸዉን አስተዋፅኦ ስናይ ከነ ዮፍታሔ ንጉሴ፣ አፈወርቅ አዳፍሬ፣ ተስፋየ ለማ ፣ አበበ ረታ፣ ልጅ አርዓያ ስላሴ ጋር በመሆን ማዘጋጃ ትያትር ቤትን መስርተዋል።  

ኢዩኤል ዮሐንስ                                        
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት በርከት ያሉ ጽሑፈ ተዉኔቶችን ደርሷል። ከነዚህም መካከል፦ የህይወት ፋና የወጣት ዜና ወይም ቸነፈር፣ ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና፣ ስራ ለሰሪዉ እሾህ ላጣሪዉ፣ ቃል ኪዳን አፍራሹ፣ የእግዚአብሔር ቸርነት የአርበኞች ጀግንነት፣ የሰዉ ሆዱ የወፍ ወንዱ የተሰኙ ረጃጅም ተዉኔቶችን ጽፏል። በተለይ ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና የተሰኘዉ ተዉኔት በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ ለ10 ተከታታይ ሳምንታት የታየና ወደ 15 የሚሆኑ ተዋንያን የተሳተፉበት ተዉኔት ነዉ። ከተዘረዘሩት ተዉኔቶች መካከል የሁለቱ ተዉኔቶች ማለትም ስራ ለሰሪዉ እሾህ ላጣሪዉና የእግዚአብሔር ቸርነት ያርበኞች ደግነት በስተቀር ሌሎቹ የተፃፉበት አመተ ምሕረት አይታወቅም። ይህ ጸሀፊ ትዉኔት ከነዚህ ረጃጅም ተዉኔቶች በተጨማሪ በሙዚቃዊ ተዉኔቶችም ይታወቃል። ከደረሳቸዉ ሙዚቃዊ ተዉኔቶች መካከል፦ ጊዜ ወርቅ ነዉ፣ አስራ ሁለት ጠቅላይ ግዛት፣ ብቸኛ የሀሳብ ጓደኛ፣ ጎልማሳዉ መንገደኛ ለፍቅር የማይተኛ፣ የሴት ፍርሀቷ እስከ መቀነቷ፣ ወንድሜ ተነስ ወፎቹ ተንጫጩ፣ አዲስ ፍቅር ያመናቅር የተሰኙ ተዉኔቶችን ደርሷል። ከአጫጭር ተዉኔቶች መካከል ደግሞ፦ ሳይቸግር ጤፍ ብድር፣ የልጃገረድ ጸሎት፣ የሰዉ ግብሩ ክብሩ፣ ዙሮ ዙሮ ሁሉም ዜሮ፣ አዳኞች ከበረሀ ሲመለሱ፣ የቀበሮ ባህታዊ እና ቀዩ ሌሊት ይጠቀሳሉ።

መላኩ በጎሰዉ
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት ከፃፋቸዉ ተዉኔቶች መካከል የተገኙት ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም፦ በ1927 ታላቁ ዳኛ እና ነይ ነይ በደመና የተሰኙ ስራዎች ይጠቀሳሉ።

አያልነህ ሙላቱ
እኒህ ደራሲ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ተዉኔቶችን ደርሰዋል። ከነዚህም መካከል፦ እሳት ሲነድ፣ የገጠሯ ፋና፣ የመንታ እናት፣ ዱባና ቅል ጥበበኛዋ ጋለሞታ ደሀ አደግ፣ ሰባራ ዘንግ፣ ድርብ ጭቁን እና ሌሎች ተዉኔቶችን ለህዝብ በመድርክ ያቀረቡ ሲሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ ዐለም፣ ቅሪት፣ ቀዝቃዛዉ ትዳር፣ ጧሪ ልጆች፣ ባልና ሚስት፣ ግርዛት፣ መስከረም፣ ቡሔ፣ የእናት ጡት፣ ያለእድሜ ጋብቻ የተሰኙ ተዉኔቶች ታይተዋል። በኢትዮጵያ ሬድዮ ደግሞ ቤተሰብ፣ ሴት ተማሪ፣ ጠለፋ፣ ዶክተር ሙሉ፣ ሴት ለጓዳ የተሰኙ ተዉኔቶችን አስደምጠዋል።

መላኩ አሻግሬ
መላኩ አሻግሬ ወደ 25 የሚደርሱ ተዉኔቶችን ጽፈዋል። ከነዚህም መካከል፦ በ1959 ሽፍንፍን፣ በ1962 አየ ሰዉ፣ በ1960 ማሪኝ፣ በ1965 ምን አይነት መሬት ናት፣ በ1954 ዐለም የተሰኙ ተዉኔቶችን ደርሰዋል። ዓመተ ምሕረታቸዉ የማይታወቁት ደግሞ ጊዜና  ገንዘብ፣ ክህደት የኑሮ ስህተት፣ የትም ወርቅ እንዳሻዉ፣ ነፍስ ይማር፣ መጥረጊያ ያለዉ፣ የእሳት ራት፣ ጉድ ፈላ፣ ግንድ አልብስ፣ ህልም ነዉ፣ ይቅርታሽን፣ ማጣትና ማግኘት፣ ባቡሩና ሌሎችም ተዉኔቶች ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹ የመላኩ ድራማዎች የኮሚዲ ዘዉግ ያዘሉ ናቸዉ።

የድራማ ባህሪያት
የድራማ ባህሪያት ድራማን ከሌሎች የሥነ ጽሑፍ ዘርፎች (ዘዉጎች) የሚለዩና የራሱ የሆኑትን ግለ ወጥ ባህሪያት እንዲላበሱ የሚያደርጉ ናቸዉ። እነሱም ዉስንና አጠቃላይ ባህሪያት ተብለዉ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ።



የድራማ ዉስን ባህሪያት
ዉስን ባህሪያት የሚባሉት የድራማን መስክ በተናጥል የሚያጠኑትን የመስኩ ምሁራንን፣ ደራሲያንን፣ ሐያሲያንን እዉቀትና ትንታኔ ሳያስፈልጋቸዉ ማንኛዉም ታዳሚ በቀላሉ ሊረዳዉ የሚችለዉ ማለት ነዉ። በዚህ መሰረትም ዉስን ባህሪያት ተብለዉ የሚጠቀሱት፦
  • በጽሑፈ ተዉኔቱ ዉስጥ ተስለዉ የሚገኙ ገጸ ባህሪያትን ሚና ወክለዉ በመድረክ ላይ የሚተዉኑ የገሀዱ ዐለም ሰዎች መኖር፣
  • በመድረክ ላይ በትወና ተግባር የተሰማሩትን ተዋንያን በአዳራሽ ተቀምጠዉ የሚመለከቱ ሰዎች መኖር፣
  • በምልልስና በድርጊት የመድረክ ክዋኔ መኖር፣
  • የተማረዉንም ሆነ ያልተማረዉን ታዳሚ እኩል ማነሳሳት ወይም ማነቃቃት መቻል፣
  • በሰዉ አዕምሮ ዉስጥ አንዳች ነገር ቀርፆ የማስቀረት ሀይሉ የላቀ መሆኑ እና ፈጣን ለዉጥ ማምጣት መቻል እና
  • የብዙ ሙያተኞች ተሳትፎ መኖር ናቸው።

የድራማ አጠቃላይ ባህሪያት
የድራማ አጠቃላይ ባህሪያት ሲባል ስለ ስነ ጽሑፍ ዘርፎች በተለይ ስለ ድራማ በቂ የሆነ የንድፈ ሐሳብ እዉቀት ኖሮት ጥበቡን መተንተን፣ ማጥናት፣ መመዘን የሚችል ሰዉ ስራዉን የሚመዝንባቸዉና በመከላከያነት የሚጠቀምባቸዉ ማለት ነዉ። እነዚህም ባህሪያት፦
  • ቀዉስ፣ ዉዥንብርና ግራ መጋባት መኖር፣
  • የተዘወተረ መሰረታዊ መዋቅር መኖር፣
  • ትኩረተ ብዙሀንን ማግኘት፣
  • ግልጽነት፣ ቀጥተኝነት፣ ለመረዳት የማያስቸግር መሆን፣
  • የተለየ የአተራረክ ብልሀት መኖር፣
  • የተለየ የታሪክ አነሳስ እና የመረጣ ፋይዳ መኖር እና
  • ተመድራኪነት ናቸዉ።

                 የድራማ አላባዉያን
1.ታሪክ
ታሪክ በማንኛዉም ተዉኔታዊ ድርጊት ወይም ክንዋኔ በቅደም ተከተል ተዘርዝሮ የሚቀመጥበት ነዉ።

ታሪክ በጊዜ ቅደም ተከተል መሰርት ከአንዱ ድርጊት ቀጥሎ የትኛዉ ድርጊት እንደሚከተል ለማሳወቅ ይረዳል። ታሪክ የክንዋኔዎች ስብስብ በመሆኑ ለማንኛዉም የፈጠራ ስራ መሰረት ነዉ ተብሎ ይታሰባል።
2.ሴራ
ሴራ በዋናነት ገጸ ባህሪያትንና ግጭትን ይይዛል። የተዉኔትን ወይም የልቦለድን አጠቃላይ ሴራ መናገር ማለት ገጸ ባህሪያት በመጀመሪያ እንዴት ግጭት ጀምረዉ እንዴት እንደሚያካርሩት ከዚያም እንዴት መፍትሔ እንደሚያገኙለት መናገር ማለት ነዉ። በአጭሩ ሴራ የምክናያትና ዉጤት ትሥሥር ነው። ሴራ በገጸ ባህሪያት መካከል ያለዉን ግንኙነት ይጠቁማል። የተዉኔት ሴራዎች ጥብቅ ሴራ፣ ልል ሴራ፣ ቁርጥራጭ ሴራና ሴራ አልባ ተብለዉ ሊከፈሉ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ዉስብስብና ነጠላ ሴራ ተብለዉ ሊከፈሉ ይችላሉ።

3.ገጸ ባህሪ
ገጸ ባህሪ ማለት በተዉኔት በልቦለድና በተራኪ ግጥም ዉስጥ ተስሎ የሚገኝ ሰዉ ነዉ። የድርሰቱ ሰዉ ስንል ሰባዊ ፍጡርን፣ እንስሳትን፣ ረቂቅ ሀሳቦችን፣ ሰማያዊ ፍጥረታትንና መናፍስትን ይጨምራል።

4.ግጭት
ግጭት በተዉኔት ዉስጥ ያሉ ገጸ ባህሪያት የሚገቡበት ቅራኔ ነዉ። በተዉኔታዊ ታሪኩ ዉስጥ የሚቀረጹ ገጸ ባህሪያት ሁሉ አብዛኛዉን ጊዜ በሶስት ጎራ ይሰለፋሉ። ግማሾቹ አቀንቃኝ ገጸ ባህሪዉን በመደገፍ ይቆማሉ፤ ግማሾቹ ፀረ አቀንቃኝ ገጸ ባህሪዉን ይወግናሉ፤ ግማሾቹ ደግሞ በመሀል ሰፋሪነት ራሳቸዉን ያስቀምጡና አንድም የአስታራቂነቱን ሚና ይወስዳሉ ወይም ከግራዉም ከቀኙም አለሁ አለሁ እያሉ በነፈሰበት በመንፈስ ይጓዛሉ። የግጭት አይነቶች ጠቅለል ባለ መልኩ ዉስጣዊና ዉጫዊ በሚሉ ሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላሉ።

5.መቼት
መቼት የተዉኔቱ ታሪክ የሚያጠነጥንበትን ጊዜና ቦታ የሚመለከት ጽንሰ ሐሳብ ነዉ። መቼትን መቼት የሚያሰኙት የድርጊቱ ጊዜ፣ የድርጊቱ ቦታ እና ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ያለዉ ማህበራዊ እዉነታ ናቸዉ። የድራማ መቼት በሁለት ይከፈላል። እነሱም ፦ ተፈጥሯዊ መቼት እና የድራማ መቼት ናቸዉ።



6.ጭብጥ
ጭብጥ በተዉኔት ዉስጥ ማዕከላዊ ወይም ገዥ የሚባለዉ ረቂቅ ሀሳብ ነዉ። ጭብጥ አካባቢያዊ እና ሁለንተናዊ በሚሉ ሁለት መሰረታዊ ክፍሎች ይከፈላል። አካባቢያዊ ወይም ወቅታዊ ጭብጥ በአንድ አካባቢ በአንድ ማህበረሰብ የሚከሰተዉን ወቅታዊ ስነ መንግስታዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎችን መሰረት ያደረገ ነዉ። በመሆኑም በተፃፈዉ ተዉኔት የሚተላለፈዉ መልዕክት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የሚያረጅ የሚያፈጅ መሆኑ አያጠራጥርም። ሁለንተናዊ ወይም አለማቀፋዊ ጭብጥ ያለዉ ተዉኔት በአንፃሩ መሰረታዊ በሆኑ የሰዉ ልጅ ምኞቶች፣ ተስፋዎች እና አዉዶች ላይ ስለሚመሰረት ለየትኛዉም ማህበረሰብና ለቀጣዮቹም ዘመናት የሚስማማና ግቡነት ያለዉ ነዉ።

የድራማ ቴክኒኮች
ተዉኔት ሲፃፍ በዉስጡ ሊይዛቸዉ የሚገባዉ ቁም ነገሮች የድራማ ቴክኒኮች ናቸዉ። የድራማ ቴክኒኮች ተብለዉ በአብዛኛዉ የመስኩ ምሁራን ዘንድ የሚታወቁትም የሚከተሉት ናቸዉ።

1.ቃለ ተዉኔት
ቃለ ተዉኔት ሁለትና ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸዉ ገጸ ባህሪያት በተዉኔት ድርሰት ዉስጥ የሚያደርጉት ምልልስ ወይም ንግግር ነዉ። በአጭሩ ቃለተዉኔት የድራማዉ ቋንቋ ነዉ ማለት ይቻላል።

ቃለ ተዉኔት ግልጽ መሆን መቻል አለበት። ቃለ ተዉኔት ግልጽ ይሆን ዘንድም የሚከተሉትን ነጥቦች ማሟላት መቻል አለበት።
  • ቋንቋዉ ሁሉም ሊያዉቀዉ የሚችል መሆን አለበት።
  • ስርዓቱን የጠበቀ የአረፍተ ነገር አወቃቀር ስራትን መከተል መቻል አለበት።
  • አረፍተ ነገሮች በተቻለ መጠን አጫጭር መሆን አለባቸዉ።
የቃለ ተዉኔት ቋንቋ የሚቀርብባቸዉ መንገዶች
  1. ምልልስ ፦ ከአንድ በላይ የሆኑ ገጸባህሪያት የሚያደርጉት የእርስበርስ መስተጋብር ነዉ።
  2. ጎንታ ፦ ፊት ለፊት ከሚነገረዉ ዉጭ የሆነ ሀሳብ ይተላለፍበታል። በጎንዮሽ የሚገለጽ የቃለ ተዉኔት አቅጣጫ ነዉ። ጎንታ አንድ ገጸባህሪ ሌሎች ገጸ ባህሪያት ባሉበት እንዳልሰሙ በመቁጠር ለተደራሲያኑ ስለ ገጸ ባህሪያት የሚናገርበት መንገድ ነዉ።
  3. ንባበ አዕምሮ ፦ አንድ ገጸ ባህሪ ብቻዉን በመድረክ ላይ የሚያደርገዉ ንግግር ነዉ።

2.ድምፀት
ድምፀት ጸሐፊ ተዉኔቱ በጽሁፈ ተዉኔቱ ዉስጥ እንዲተላለፍ የሚፈልገዉ የአስተሳሰብ መንፈስ ነዉ። የአንድ ተዉኔት አጠቃላይ ድምፀት ያለፈ ጊዜ የደስታና የሀዘን ትዝታ፣ የመረረና የጠየመ ገጠመኝ፣ አስቂኝ ክስተት፣ ምፀታዊ ስሜት ወይም ሌላ አስተሳሰብ እንዲንጸባረቅበት ተደርጎ በደራሲዉ ሊቀርብ ይችላል። በተዉኔቱ ዉስጥ እያንዳንዱ ቃለ ተዉኔት ቃል፣ ሀረግ ወይም ዓረፍተ ነገር መድረክ ላይ በተዋንያን በሚነገር ጊዜ የራሱ የሆነ የጥራት፣ የምት፣ የአነሳስ፣ የአጣጣልና የጥንካሬ ድምፀት መኖሩ በሚገባ ይታያል። የእያንዳንዱ ተዋናይ ቃለ ተዉኔት ለዋናዉ ሀሳብ የሚገብር ቢሆንም የቁጣ፣ የወኔ፣ የጉጉት ፣ የፍርሀት፣ የሀዘን፣ የትዕዛዝ፣ የዉግዘት፣ የቁጭትና የመሳሰለዉ ድምፀት መያዙ በግልፅ ይታወቃል። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ድምፀት የአስተሳሰብ መንፈስንና የቃል ወይም የድምጽ አወጣጥ ፀባይን አመልካች ሆኖ እናገኘዋለን።
3.ድባብ
ድባብ ማንኛዉም ተዉኔት በተደራሲያን ልቦና ዉስጥ የሚፈጥረዉ አስደሳች ወይም አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ ወይም አጓጊ ስሜት ሲሆን ከድምፀት ግን ይለያል። ድምፀት በልዩ ልዩ ስሜቶች ላይ መሰረት በማድረግ ደራሲዉ የሚያስተላልፈዉ የአስተሳሰብ መንፈስ ነዉ። ይህም እንደ ድባብ በየገቢሩና በየትይንቱ የሚቀያየረዉን ስሜት ብቻ ሳይሆን በተዉኔቱ መጨረሻ ተመልካች በልቦናዉ ይዞት የሚሄደዉን ገዥ ስሜት ይጨምራል። የአንድ ተዉኔት ድባብ የትዕይንት ለዉጥ በተደረገ ቁጥር አብሮ የሚለወጥ ነዉ። የመጀመሪያዉ ትዕይንት ጨፍጋጋ ድባብ ቢኖረዉ ቀጣዩ ትዕይንት ደስ የሚል ድባብ ሊኖረዉ ይችላል። የአንድ ተዉኔት ድባብ በየትዕይንቱ ለዉጥ የማያሳይ ወይም የማያመጣ ከሆነ በተደራሲያን ዘንድ አሰልች ስሜት መፍጠሩ የማይቀር ይሆናል።

4.ዘልማድ
ዘልማድ ማለት ተደራሲያን አንድን ኪነጥበባዊ እዉነታ በገሀዱ ዐለም እዉነታ አምሳያነት የሚቀበሉበት ስምምነት ነዉ። ድራማ ስኬታማ እንዲሆን እንደ ሌሎች የስነ ጽሁፍ ስራዎች ሁሉ የተወሰኑ ዘልማዶችን መያዝ ይኖርበታል። በድራማ ጥበብ ማንኛዉም ከእዉነተኛዉና ተጨባጩ ህይወት የተለየን ነገር ሁሉ ይጨምራል። በግሀዱ ዐለም በሶስትና በአራት ሳምንታት መፈፀም የሚኖርበት ድርጊት በድራማዊ ታሪኩ በሰዓታት ልዩነት እንዲከወን ቢደረግ በተደራሲያን ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘዉ በዘልማድ ነዉ። በድራማዉ ከመድረኩ መጠን ጋር ሊስተካከሉ የማይችሉ መቼቶችን ከመኖሪያ ቤት ዉጭ ያሉ መቼቶችን ማለትም እንደ የጦር ሜዳ፣ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ፣ በረሀ፣ የወንዝ ዳርቻ ወዘተ ያሉትን በተዋንያን አንደበት እንዲነገሩ በማድረግ ለተመልካቹ ማሳወቅ ይቻላል። ተመልካቹም በዘልማድ ይቀበለዋል። እንደ ድራማዊ ቦታ ሁሉ ድራማዊ ጊዜም በዘልማድ ሊቀርብ ይችላል። የድራማዉ ልዩ ልዩ ድርጊቶች በሰዓታት፣ በቀናት፣ በወራት፣ በዓመታት እየተጠቃለሉ ሲቀርቡልን ያለምንም ተጠየቅ አሜን ብለን የምንቀበለዉ በድራማዊ ጊዜዉ ዘልማድ ነዉ።

5.ገቢር
የአንድ ድራማ ድርሰት ዐቢይ ወይም ዋና ክፍል ነዉ። በንዑስ ምዕራፎች ሲከፋፈል ደግሞ ትዕይንት ይባላል። ልቦለድ በምዕራፍና በንዑስ ምዕራፍ እንደሚከፋፈል ድራማም በገቢርና በትዕይንት ይከፋፈላል። ከአንድ ገቢር ወደ ሌላ ገቢር ለዉጥ በሚኖርበት ጊዜ ብዙዉን ጊዜ የቦታና የጊዜ ለዉጥ ይኖራል። የትዕይንት ለዉጥ ደግሞ አብዛኛዉን ጊዜ የሚከናወነዉ አንድ ራሱን የቻለ ድርጊት ወደ ሌላ ራሱን የቻለ ድርጊት ሽግግር ሲያደርግ ሲሆን በትዕይንት ለዉጥ ጊዜ እንደ ገቢር የቦታና የጊዜ ለዉጥ የለም። በትዕይንት በአብዛኛዉ የጊዜ ለዉጥ ይኖራል። የትዕይንት ለዉጥ አነስተኛ ነዉ። በገቢር ሰፋ ያለ ለዉጥ ይኖራል። ለዉጡን ለማካሄድም ለተወሰኑ ሰከንዶች የመድረኩን መብራት በማጥፋት ሊካሄድ ይችላል። ፀሀፊ ተዉኔቱ ድራማዉን በገቢርና በትዕይንት የሚከፋፍለዉ በዘፈቀደ ሳይሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነዉ። በቂ ምክናያትም ሊኖረዉ ይገባል።

የአንድ ድራማ መቼት ከመጀመሪያዉ እስከ መጨረሻዉ አንድ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም የመቼት ለዉጥ ሲኖር ገቢሩም ይለወጣል። ለዉጡን ለማመልከትም የመድረኩን መልክና በአካባቢዉ የሚገኙ ቁሳቁሶችን መለወጥ ያስፈልጋል። በዚህ ጊዜ መጋረጃ ለተወሰኑ ሰከንዶች ወይም ደቂቃዎች ይዘጋል። አንድ ድራማ በገቢር ከሚከፋፈልባቸዉ ምክናያቶች መካከል ሌላዉ ደግሞ ሁሉንም ታሪክ በአንድ በተወሰነ ጊዜና ቦታ ማቅረብ ለታዳሚያን አሰልች ስለሚሆን መለዋወጡ አስፈላጊ ነዉ። አብዛኛዉን ጊዜ አንድ ገቢር በትዕይንት የሚከፋፈለዉ የጊዜ ለዉጥ ሲኖር ነዉ ብለናል፤ አልፎ አልፎ ግን በዚያዉ መቼት ዉስጥ ያለቦታ ለዉጥ ማለትም ከሳሎን ወደ መኝታ ክፍል፣ ከመኝታ ክፍል ወደ ሳሎን የመሳሰሉ መጠነኛ ለዉጦች ሲኖሩት ሊለወጥ ይችላል።

አንድ ድራማ ይህን ያህል ገቢርና ይህን ያህል ትዕይንት ይኑረዉ ብሎ መናገር አይቻልም። ምክናያቱም የገቢሩም ሆነ የትዕይንቱ ቁጥር ድራማዉ እንደተፃፈበት ዘመንና እንደ ፀሀፊ ተዉኔቱ ይለያያል። ቀደም ባለዉ ጊዜ ተዉኔቶች በአራትና በአምስት ገቢሮች ይከፋፈሉ ነበር። በቅርብ ዘመን ግን የገቢሮች ቁጥር ከሶስት አይበልጥም። ተዉኔቱን ባለአንድ ገቢር አድርጎ በትዕይንቶች መከፋፈልም እየተለመደ መጥቷል።


የድራማ ዘዉጎች ወይም አይነቶች
የድራማ አይነቶች ትራጀዲ፣ ኮሚዲ፣ ድንቃይና ቧልታይ ተብለዉ በአራት ይከፈላሉ።

ትራጀዲ ወይም መሪር ድራማ
ጭፍግ ወይም  አሳዛኝ የድራማ ዘዉግ እየተባለም ይጠራል። ድባቡም ፍርሀትን፣ ሰቀቀንን፣ ሀዘንን ይዘራል። በርካታ ምሁራን ትራጀዲ ድራማ በአሳዛኝና በሰዉ ልጆች መሰረታዊ ችግር (ስነልቦናን እና ሞራልን) በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መመስረት አለበት ብለዉ ያምናሉ። የሰዉ ልጅ መሰረታዊ ችግር የሚባሉትም የሰዉ ልጅ የሞራል፣ የስነልቦናና የቀን ከቀን ማህበራዊ ግንኙነቶች የተመሰረቱ ፈታኝና ጠቋሚ ጥያቄዎች ያነሳሉ። የትራጀዲ ድራማ ግጭቶች አሳዛኝና መሰረታዊ በሆኑ ችግሮች ላይ ይመስረቱ እንጅ መፀነስ ያለባቸዉ በሰዉ ልጅ ሁለት ስሜቶች ማለትም በደስታና በሀዘን ስሜቶች መካከል መሆን አለበት። የትራጀዲ ድራማ ግጭቶች የሚፀነሱትና እየከረሩ የሚመጡት አቀንቃኝ ገጸ ባህሪዉ በዉስጣዊ ግጭት ወይም በዉጫዊ ግጭት ዉስጥ ገብቶ በሚያደርገዉ ትግል ነዉ። ይህ ዘዉግ በተደራሲያን ዘንድ አሳዛኝ ስሜት የሚፈጥረዉም የተቀረፀዉ አቀንቃኝ ገጸ ባህሪ በየዋህነት ከገባበት ቅራኔ ዉስጥ መዉጣት ሲሳነዉ በመጨረሻም በገጸ ባህሪዉ አሰቃቂ ዉድቀት ወይም አሟሟት ሲደመደም ነዉ። አቀንቃኝና ፀረ አቀንቃኝ ገጸ ባህሪያትን ጨምሮ በትራጀዲ ድራማ ዉስጥ የሚቀረጹትን ገጸ ባህሪያት በተመለከተ ከ18ኛዉ ክፍለ ዘመን በፊት የተለየ ድራማዊ ዘልማድ ነበር። ይኸዉም አቀንቃኝ ገጸ ባህሪያት በማህብረርሰቡ ዉስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸዉ ታላላቅ ሰዎች እንደ ነገስታት፣ የጦር አዛዦች፣ ልዑላን፣ ባለፀጎች የመሳልሰሉት እንዲሆኑ ይደረግ ነበር። ከ18ኛዉ ክፍለዘመን በኋላ ግን ይህ ዘልማድ ተለዉጦ በሚፃፈዉ ትራጀዲ የሚቀረጹት ገጸ ባህሪያት የመካከለኛና የዝቅተኛ መደብ አባላትንም ይጨምራል። የዕድሜ፣ የፆታና የማህበራዊ ደረጃ እንደ መመዘኛ ሳይወሰድ የትኛዉንም የማህበረሰብ ክፍል መቅረጽ እየተለመደ መጥቷል። በአሮጌዉም ሆነ በአዲሱ ዘልማድ በትራጀዲ ድራማ ዉስጥ የሚቀረፀዉ አቀንቃኝ ገጸ ባህሪ መልካም ዐመል ወይም ምግባር ያለዉ ተደርጎ እንዲሳል ይጠበቃል። ይህም ሲባል ግን አቀንቃኝ ገጸ ባህሪዉ አንድ አይነት ድክመት አብሮት መፈጠሩ አይቀርም። ለድራማዊ ግጭቱ መንስኤዉም ይኸዉ ድክመቱ ይሆንና ለሽንፈት እንዲዳርገዉ ሆኖ ይቀርባል።

የትራጀዲ ድራማ አይነቶች
1.ጥንታዊ ትራጀዲ
ይህ የድራማ ዘዉግ የራሱ የሆነ የአላባዉያን አቀራረጽ አለዉ። ታሪኩ በተወሰነ ጊዜና ቦታ የሚፈፀም ነዉ። የጠበቀ አንድነት ያለዉ፣ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ሳይጠማዘዝና ቅርንጫፎች ሳይኖሩት የሚጓዝ ነዉ። በገጸ ባህሪ አሳሳል በኩል ደግሞ በተለይ ዋናዉ ገጸ ባህሪ የተከበረ ሰዉ እንዲሆን ይደረጋል። ቢሆንም ስህተት ከመፈፀም አያመልጥም። ይህም ስህተቱ ቢሌሎች በሚቀርቡት ገጸ ባህሪያት ይነገርዋል። ይሁን እንጂ ከራሱ በላይ የሚያምነዉ ስለሌለና እጅግ በራሱ ስለሚተማመን ሌሎች የሚናገሩትን አይሰማም። በዚህም የተነሳ ለዉድቀት ይዳረጋል። ከዚህ በኋላ ነዉ የሰራዉ ስራ ትክክል አለመሆኑን የሚረዳዉ። ነገር ግን ይህ የሚሆነዉ በታሪኩ ዉስጥ በጣም ዘግይቶ በመሆኑ ከዉድቀት አይድንም። ስህተቱን ቀስ በቀስ ማህበረሰቡ የጣለበትን ቅጣት እየተቀበለ እየተሰቃየ በመከራ ዉስጥ ተዘፍቆ ይረዳዋ። በዚህ ስህተቱና ዉድቀቱ የተነሳ ከደስተኛነት ወደ ሀዘንተኛነት፣ ከነበረዉ ከፍተኛ ክብር ዝቅ ወዳለ ደረጃ ይወርዳል። በዚህ ሁኔታ ለዉድቀትና ለመከራ የተዳረገዉ ገጸ ባህሪ የሌሎችም እድል ከርሱ ጋር የተቆራኘ ስለሚሆን በርሱ ምክናያት በሚመጣዉ መከራ ሌሎችም ገጸ ባህሪያት ይሰቃያሉ። ሴራዉን ስንመለከት ነጠላና የጠበቀ አንድነት ያለዉ ነዉ። ማለትም ምክናያትና ዉጤቱ ቅርንጫፎች አይበዙበትም። ዐቢይ ገጸ ባህሪዉ የሚገጥመዉ መራራ ፈተና ከአንድ ዋና ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነዉ። ለዚህ ዐቢይ ጥያቄ የሚሰጠዉን መልስ ለማፈላለግ በሚደረግ ጥረት ዉስጥ ሴራዉ እዉን ይሆናል።

ጥንታዊ ትራጀዲ ወጥ የአወቃቀር ስራትን ይከተላል። ማለትም መነሻ፣ መካከልና መጨረሻ ይኖረዋል። ይህ ባህሪዉ ከሞላ ጎደል ቋሚ ነዉ።  በዚህ እድገት ዉስጥ ሴራዉ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል። ችግሮችና እንግልቶች ከመነሻዉ ጀምረዉ እየተወሳሰቡ፣ እየጦዙና እንደገናም እየረገቡ ወደ ልቀት ያዘግማሉ። ይህ የአወቃቀር ባህሪዉ በተለይ በዋና ገጸ ባህሪዉ አቀራረጽ ላይ ጎልቶ እንዲታይ ይደረጋል። ሌላዉ የጥንታዊ ትራጀዲ ባህሪ አሰቃቂ ክንዉኖች ከመጋረጃ ጀርባ ይፈፀማሉ። የከፋ አካላዊ ስቃይ፣ ሞት ወይም ሌሎች ህሊናን የሚሰቀጥጡ ሁነቶች በመድረክ ላይ አይከናወኑም። ከመጋረጃዉ ጀርባ እንዲከናወኑ ይደረግና ዉጤታቸዉ ብቻ በገጸ ባህሪያት አንደበት ለታዳሚያን ይነገራል። ይህ የትራጀዲ ዘዉግ ላቅ ያለ ምናባዊነት የሚታይበት ነዉ። ዋናዉ ገጸ ባህሪ የሚቀረጸዉ ከከፍተኛ መደብ በመሆኑ የዚህ መደብ አባላት ከሚታወቁበት ነገር አንዱ ደግሞ ፍልስፍናቸዉና ቋንቋቸዉ ነዉ። የማሳመን ግርማሞገስ የመደመጥ ሀይል አላቸዉ። ቋንቋቸዉ ጠንካራ ነዉ። ስለሆነም ዐቢይ ገጸ ባህሪዉ ሲሳል ይህን እዉን አድርጎ እንዲመጣ ይደረጋል። መቼታቸዉም ያሸበረቀና ከዘወትር ቦታዎች የተለየ ነዉ።  

2.ኤልሳቤጣዊ ትራጀዲ
ይህ ዘዉግ የተከሰተዉ ደግሞ በዳግም ልደት ወቅት ነዉ። ማለትም በእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤጥ የንግስና ዘመን ከ1558-1603 የተከሰተ ነዉ። ይህ ዘመን በተለይም በእንግሊዝ ድራማ ወርቃማ ዘመን እየተባለ ይጠራል። ስያሜዉን ያገኘዉም ንግስት ኤልሳቤጥ በወቅቱ በህዝቧ ዘንድ እንደ አርዓያና ተምሳሌት ከመታየቷ በተጨማሪ ለጥበባዊ ስራዎች ፍቅር እንደነበራትና ታበረታታ እንደነበር ይነገራል። ይህ የድራማ አይነት በ16ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበሩትን የሸክስፒርንና መሰል ድራማዎችን የሚያካትት ነዉ። የዚህ ድራማ ታሪክ በተወሰነ ጊዜና ቦታ የሚከናወን አይደለም። ሴራዉም ቢሆን እንደ ጥንታዊዉ የጠበቀ አይደለም። ዐቢዩ ገጸ ባህሪ እንደ ጥንታዊዉ ትራጀዲ ከከፍተኛ የማህበረሰብ መደብ የወጣ፣ የተከበረ፣ በሳል፣ አዋቂ የሚባል አይነት ነዉ። ለዉድቀቱ ምክናያት የሚሆነዉም ከመጠን በላይ በራስ መተማመን፣ ትዕግስት ማጣት፣ ርምጃ ለመዉሰድ መቸኮልና የመሳሰሉት ናቸዉ። የዚህ ድራማ ገጸ ባህሪ ስህተቱን የሚረዳዉ እንደ ጥንታዊዉ ሁሉ ነገሩ ካለፈ በኋላ በመሆኑ ከዉድቀት አያመልጥም። በዚህም የተነሳ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ርምጃ ይወስዳል።

ኤልሳቤጣዊ ትራጀዲ እንደ ጥንታዊው ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ታዳሚዉን በጭንቀትና ፍርሀት ዉስጥ ከቶ የሚያልቅ ሳይሆን አልፎ አልፎ ይህ ሁኔታ ለዘብና ላላ የሚልበት አጋጣሚ ያለዉ የትራጀዲ አይነት ነዉ። የዚህ ድራማ ሌላዉ ባህሪ የድርጊትን፣ የታሪክንና የክንዋኔን አንድነት የግድ አይጠብቅም። ሌላዉ እንደ ጥንታዊዉ ትራጀዲ ዐቢይ ገጸ ባህሪዉ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ በሚጠመድ መሰናክል ዉስጥ ብቻ አይደለም ተሰናክሎ የሚወድቀዉ። የሚያጋጥሙት ችግሮች ደግሞ ቶሎ ለመፍታት የሚወስደዉን ርምጃ ጥቅምና ጉዳት አመዛዝኖ ለመወሰን ቀላል አይሆንለትም። ስለዚህ በጣም በተወሳሰበ አዕምሯዊ ቀዉስ ዉስጥ ተዘፍቆ ይታያል። በዚህ ድራማ ዘግናኝ ክንዋኔዎች በመድረክ ላይ መፈፀማቸዉ ሌላዉ ተጠቃሽ ባህሪ ነዉ። ይህ ማለት ማንኛዉም ቁልፍነት ያለዉ አሰቃቂና ዘግናኝ ርምጃ በታዳሚዉ ፊት ይፈፀማል።

3.ዘመናዊ ትራጀዲ
የዚህ ድራማ መከሰቻ 19ኛዉ ክፍለ ዘመን ሲሆን እስካሁኑ ዘመን ድረስ ዘልቋል። የዚህ ድራማ ትኩረት በ19ኛዉ ክፍለ ዘመን የተከሰቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አመለካከቶች ላይ ነዉ። በተለይ ደግሞ ተፈጥሯዊነትና እዉናዊነት የሚባሉት የኪነጥበብ ፈለጎች ካሳደሩት ተፅዕኖ የመነጨ መሆኑ ይነገራል። የዘመናዊ ትራጀዲ ገጸ ባህሪያት ፈተናና መከራ የሚደርስባቸዉ፣ ከነሱ ከላቀ ሀይል ጋር የሚታገሉ በዚህም ይበለጥ ችግር ዉስጥ የሚገቡ ናቸዉ። ከችግራቸዉ ለመዉጣት በተፍጨረጨሩ ቁጥር ችግሮቻቸዉ ይበልጥ እየተጠናከሩባቸዉ ይሄዳሉ። በዚህ መልክ መቅረቡ ደግሞ ድራማዉን አስጨናቂና አሸባሪ ያደርገዋል። ይህ ድራማ የሁለቱን ትራጀዲ ድራማዎች ግጥማዊነት አይከተልም። የሚፃፈዉ በዝርዉ ነዉ። ይህ አመለካከትም ሰዎች በእዉኑ ህይወታቸዉ በግጥም ስለማይግባቡ ወይም ስለማይነጋገሩ ገጸ ባህሪያት ደግሞ የእዉኑ ዓለም ሰዎች ወኪል በመሆናቸዉ በዝርዉ መነጋገር አለባቸዉ ከሚል አመለካከት የመነጨ ነዉ።

ኮሚዲ ወይም ኢመሪር ድራማ
ኮሚዲ የሰዉን ልጅ ማህበራዊ ወይም ግላዊ ህፀፅና ዐመልን እየተቸ፣ እየነቀፈ፣ እያሽሟጠጠ ለማረም ወይም ለማስተካከል የሚሞክርና ተደራሲያንንም እያሳቀ ቁም ነገር የሚያስጨብጥ የድራማ ዘዉግ ነዉ። ኮሚዲ ተመልካችን የማያስጨንቅ፣ ብሩህ ድባብ የሰፈነበት፣ ፈገግ እያሰኘ ወይም እያሳቀና እያንከተከተ ቁም ነገር የሚያስጨብጥ እንጂ ለማሳቅ ብቻ ሲባል የሚዘጋጅ አይደለም፡፡ ይህ ድራማ ይበልጥ የሚያነጣጥረዉ በአንድ ማህበረሰብ ዉስጥ በሚታዩ ድክመቶች ላይ ነዉ። ድክመቶችን በገጸ ባህሪያት አኗኗር በማሳየት አቃቂራዊ በሆነ መልክ ወደ መድረክ ያቀርባቸዋል። አላማዉም እነዚያን ማህበራዊ ጉድለቶች ማረምና ማህበራዊ ቀዉስን ማስወገድ ነዉ። የኮሚዲ ድባብ የተረጋጋና ተስፋ የሚሰጥ ነዉ።

የኮሚዲ ድራማ ዘመን ተሻጋሪነት ወይም ዘላቂነት ከትራጀዲ ጋር ሲነፃፀር ደካማ ነዉ። ምክናያቱም ኮሚዲ ድራማ በአንድ በተወሰነ ቦታና ጊዜ በሚገኝ ማህበረሰብ ባህል፣ ወግና ልማድ እንዲሁም ዕሴት ላይ የሚያተኩር ነዉ። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ብዙ ጊዜ ዘላቂነት የሌላቸዉ ለተወሰነ ጊዜ ቆይተዉ የማህበረሰቡን ዕድገት እየተከተሉ የሚሻሩና የሚለወጡ በመሆናቸዉ ድራማዉን ዘመን ተሻጋሪ እንዳይሆን ያደርጉታል። የኮሚዲ ድራማ ገጸ ባህሪያት በትራጀዲ ድራማ ዉስጥ እንደምናገኛቸዉ አይነት በማህበረሰቡ ዉስጥ ያላቸዉ ቦታ ከፍ ያለና በአመለካከታቸዉም የጠለቁ አይደሉም። በየትኛዉም የማህበረሰብ ክፍል የምናገኛቸዉ ዘወትራዊ አይነት ናቸዉ። ቋንቋዉም እንደትራጀዲ ያሸበረቀ፣ የታመቀና የተጋነነ አይደለም። የኮሚዲ ድራማ ሴራ ብዙ ጊዜ የጠበቀ አንድነት የለዉም። ማለትም ታሪኩ በጠበቁ ምክናያትና ዉጤት ትስስሮሽ ሳይሆን በአጋጣሚዎች የተገነባ ነዉ። ማለትም ለገጸ ባህሪያት ዉድቀት የሚሆነዉ ምክናያት በግልፅ የሚታይ አይደለም። በትራጀዲ ድራማ ግን ምክናያት በግልጽ ሊታይ ይችላል።

ቧልታይ ወይም ፍርስ ድራማ
ይህ ድራማ ሳቅን በተጋነነ ሁኔታ ለማጫር ተብሎ የሚፃፍ፣ የተጋነኑ እዉነቶችና ድርጊቶች ተደራርበዉ የሚመጡበት፣ ገጸ ባህሪያት ብዙ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ የሚታዩበት ነዉ። በድራማዉ ዉስጥ ገጸ ባህሪያት እርስበርሳቸዉ ሲደባደቡ፣ ከግድግዳ ጋር ሲላተሙ፣ እቃ ሲሰብሩና ሲያተራምሱ ይታያሉ። የዚህ ድራማ ዋነኛ ግብ በዚህም በዚያም ብሎ ሳቅን መፍጠር ነዉ። የማይመሳሰሉ አንዳንዴም ሊሆኑ የማይችሉ ተግባሮች ወደ መድረክ መጥተዉ በተዳሚዉ ዘንድ ሳቅ እንዲቀሰቅሱ ይደረጋል። ገጸባህሪያቱን ወክለዉ የሚቀርቡ ተዋንያን ላቅ ያለ የቀልደኝነት፣ የቅልጥፍናና የአስቂኝ ችሎታ ሊኖራቸዉ ይገባል። እንዲያዉም በቧልታይ ድራማ ዉስጥ ፀሀፊ ተዉኔቱ ካለፈባቸዉ ጉዳዮች ይልቅ ተዋንያኑ የሚያሳዩት የቧልተኝነት፣ የፌዘኝነት ወይም የአስቂኝ ችሎታ ድርሻ አለዉ። ሌላው በቧልታይ ድራማ ዉስጥ የሚስተዋለዉ ነገር ወከባ ይበዛበታል። ድርጊቶች የሚከናወኑት ባልተጠበቀ ፍጥነት ነዉ። በአጠቃላይ የዚህ ድራማ ድባብ ርጋታ የሌለዉ፣ በትዕግስት የሚፈፀም ነገር የማይስተዋልበት ነዉ። ክዋኔዎች በተደጋጋሚ የሚቀርቡበት ያልተጠበቁ ጉዳዮች የሚቀርቡበት ነዉ።

ድንቃይ ወይም ሜሎ ድራማ
የትራጀዲና ኮሚዲ ባህሪያትን አቀላቅሎ ይዞ የሚገኝ የድራማ ዘዉግ ነዉ። ከትራጀዲ ጋር የሚያመሳስለዉ አሳዛኝ ርዕሰ ጉዳይ ማንሳቱ ሲሆን ፍርሀቱና ጭንቀቱ ግን እንደ ትራጀዲ የጎላ አይደለም። ከኮሚዲ ጋር የሚያመሳስለዉ ደግሞ አጠቃላይ ድራማዊ ግጭቱ በስተመጨረሻ በአስደሳች መልኩ እልባት ማግኘቱ ነዉ። ገጸ ባህሪያቱ በተደጋጋሚ ከባድ አደጋ ሲገጥማቸዉና ከአደጋዉ በአስገራሚ ሁኔታ ሲያመልጡ ሲያሸንፉ ይታያሉ። በዚህ ድራማ ሰናዩ ገጸ ባህሪ መልካም እንደሆነ ይዘልቃል። በመጨረሻም መልካም ነገር ያገኛል። ዕኩዩ ደግሞ መጥፎ እንደሆነ ይቀራል። ወይም የባሰ ዕኩይ ይሆናል። ሁሉም እንደ ስራዉ ይከፈለዋል፡፡ ያጠፋዉ ይቀጣል፤ ያለማዉ ይሸለማል።

የመድረክ ድራማ
የመድረክ ድራማ ከቴሌቪዥን ድራማና ከሬድዮ ድራማ ከሚለይባቸዉ ባህሪያት አንዱ ህይወታዊ ዝግጅት መሆኑ ነዉ። ህይወታዊ ዝግጅት ሲባል በመድረክ የሚቀርበዉ ድራማዊ ታሪክ ዐይነ ግቡና ጆሮ ግቡ ከመሆኑም በተጨማሪ ተዋንያን ትርኢቱን በተመልካች ፊት በአካል ቀርበዉ ከማሳየታቸዉ ጋር ይያያዛል። ይህም ማለት የሚቀርበዉ ዝግጅት እንደ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድራማ ዝግጅቶች ሁሉ ተቀርፆ የሚቀርብ አይደለም። ሌላዉ የመድረክ ድራማ ባህሪ የቦታ፣ የጊዜና የድርጊት ቁጥብነት እንዲኖረዉ ሆኖ የመፃፉ ጉዳይ ይሆናል። ደራሲዉ ድራማዉ የሚመደረክበትን ጠባብ መድረክ ከግምት ዉስጥ በማስገባት የድርጊቱን መከናወኛ ቦታ፣ ድርጊቱ የሚከናወንባቸዉን ጊዜያት እና የሚከናውነዉን ድርጊት መርጦና አሳጥሮ ያቀርባል። የመድረክ ድራማ ተመልካች በቁጥር ከሬድዮና ቴሌቪዥን ድራማ ተመልካች በእጅጉ ያንሳል። ታዳሚዉም እንደ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድራማ ተደራሲ ዝግጅቱን የሚያዳምጠዉ በአጋጣሚ ሳይሆን ስራየ ብሎ የመግቢያ ክፍያ ከፍሎ በመግባት ነዉ።

የሬድዮ ድራማ
ከልቦለድ ድርሰት በሚመሳሰል መልኩ በሬድዮ ድራማ የሚሳሉ ገጸ ባህሪያት ከመደመጣቸዉ በቀር በአካል ገዝፈዉ አይታዩም። የሬድዮ ድራማ ከመድረክ ድራማ ጋር ሲነፃፀር በመቼት ገለፃ፣ በገጸ ባህሪያት ቀረፃ፣ በቋንቋ አጠቃቀም፣ በታሪኩ እጥረትና እርዝማኔ፣ በአዘገጃጀት፣ በትወና እና በተመልካች ተፈጥሮ ረገድ የሚከተሉት ባህሪያት ይንፀባረቁበታል።
  1. ተደራሲያን የሬድዮ ድራማዉን የሚከታተሉት የተዋንያንን ንግግር እያዳመጡ ስለሆነ በድራማዉ ዉስጥ የሚሳሉት ገጸ ባህሪያት ቁጥር የተመጠነ እንዲሆን ይጠበቃል። አድማጭ አንዱን ገጸ ባህሪ ከሌላዉ ገጸ ባህሪ የሚለየዉ በድምጹ ቅላጼ፣ በዳተኝነቱና በፈጣን ንግግሩ፣ በድምጽ አነሳስና አጣጣሉ ነዉ። ስለሆነም የገጸ ባህሪያት ብዛት በቁጥር በጨመር አጋጣሚ ሁሉ ሚናቸዉና ድምፃቸዉ ተመሳስሎ ስለሚኖረዉ አድማጭ አንዱን ከአንዱ ለመለየት ይቸገራል።
  2. የሬድዮ ድራማ ተደራሲ ቆም ብሎ ለማሰላሰል ጊዜ ስለሌለዉ የድራማዉ ቋንቋ አመራማሪ፣ ፍልስፍና ነክና ሲበዛ የአንድን የስራ መስክ መሰረት ያደረገ መሆን የለበትም። የሬድዮ ድራማ ታሪኩ የሚራመደዉ፣ የመቼት ለዉጥ መኖሩ የሚታወቀዉ፣ የገጸ ባህሪያት አካላዊ አቋም የሚገለፀዉ በቃለ ተዉኔቱ ስለሆነ የድራማዉ ቋንቋ ወሳኝነት አለዉ። የሬድዮ ድራማ ቃለ ተዉኔት በተደመጠ ጊዜ አድማጩ ያለምንም ችግር ሊረዳዉ መቻል አለበት። የድራማዉ ቋንቋ የዕለት ከዕለት ንግግር መምሰል አለበት። የገጸ ባህሪያት ንግግርም አጭርና ግልጽ መሆን አለበት።
  3. የሬድዮ ድራማ ታሪክ፥ እጅግ በጣም ረጅምና ተከታታይነት ያለዉ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ዘርፍ ታሪኮችን እየዘረዘረ አይሄድም። ማለትም ከአንድ በላይ ሴራዎችን ማስተናገድ አይኖርበትም። ታሪኩ የመደመጥ ዕድል እንዲኖረዉ ነጠላ ሆኖ በልብ ሰቀላ የተሞላ መሆን አለበት።
  4. በሬድዮ ድራማ የሚቀረጸዉ መቼት እንደ መድረክ ድራማ ቁጥብነት ያለዉ ወይም አንድነቱን የጠበቀ እንዲሆን አይፈለግም። የሬድዮ ድራማ መቼት ቶሎ ቶሎ የመለዋወጥ ሙሉ ነፃነት ስላለዉ የጊዜና የቦታ ለዉጥን በተመለከተ በአንድ ድራማዊ ታሪክ ዉስጥ በተፈለገዉ ቁጥር ሊቀነስ ወይም ሊጨመር ይችላል።
  5. የሬድዮ ድራማ ተደራሲ እንደ መድረክ ድራማ ተመልካች ሙሉ ጊዜዉን ሰዉቶ ስራየ ብሎ ሳይሆን የሚከታተለዉ አንድ ተግባር እያከናወነ ወይም በመንገድ እየተጓዘ አሊያም ከአልጋዉ ላይ ጋደም ብሎ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም የሚተላለፈዉ ድራማ ተደራሲዉ ከያዘዉ ተደራቢ ስራ የበለጠ ማራኪ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። ታሪኩ ማራኪ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ፣ ዝግጅቱም የተዋጣለት እስከሆነ ድረስ የሬድዮ ድራማ አድማጭ በቁጥር አቻ አይገኝለትም። በገጠር፣ በከተማ፣ በመኖሪያ ቤት፣ በመስሪያ ቤት፣ በእግር ጉዞ፣ በመኪና ጉዞ፣ በጥበቃ ስራ ላይ ያለ እና ሌላዉም ሙያተኛ ሁሉ በአንድ ጊዜ ሊከታተለዉ ይችላል።
  6. በሬድዮ ድራማ ዝግጅት እንደ መድረክ ድራማ ዝግጅት የዕነፃ ስራ፣ የአልባሳት፣ የመዋቢያ፣ የመድረክ ዳራዊ ቅብ፣ የመብራት ስርጭትን የሚመለከቱ ወጭዎች ስለማይኖሩ የሬድዮ ድራማን ለማዘጋጀት ከባድ ወጭ አይጠይቅም፡፡ ምናልባት ወጭ አለ ከተባለ ለግብአተ ድምፅ ማቀነባበሪያ መጠነኛ ገንዘብ ሊጠይቅ ይችላል።

የቴሌቪዥን ድራማ
እንደ መድረክ ድራማ ሁሉ ዐይነ ግቡና ጆሮ ግቡ ነዉ። ሆኖም ግን የቴሌቪዥን ድራማ ከመድረክ ድራማ የሚለይባቸዉ ነጥቦች አሉ። በቴሌቪዥን ድራማ በመድረክ ድራማ ከምናገኛቸዉ ከሶስቱ የሙያ ዘርፎች ከድርሰት፣ ከዝግጅትና ከትወና የስራ ዘርፎች በተጨማሪ የካሚራ ጥበብ ይታከልበታል። በቴሌቪዥን ድራማ የሚቀረፀዉ መቼት እንደ መድረክ ድራማ መቼት የተገደበ አይደለም። የቴሌቪዥን ድራማ እንደ መድረክ ድራማ ህይወታዊ አይደለም። ተቀርፆ የሚተላለፍ በመሆኑ ተዋንያንና ተመልካቹ በግንባር የመገናኘት ዕድል የለቸዉም። የቴሌቪዥን ድራማ ከመድረክ ድራማ፣ ከሬድዮ ድራማና ከፊልም ጥበብ የተወሰኑ አላባዎችን አዉጣጥቶ የያዘ ነዉ።

ፊልም
ፊልም ከኪነጥበብ ዘርፎች አንዱ ሲሆን በዉስጡ ብዙ አላባዉያንን ይዞ ይገኛል። ፅሁፈ-መቅረጸ ምስል (ፊልም ስክሪፕት)፣ መቅረጸ ብርሀን (ካሜራ) እና ግብአተ ድምፅ በዐቢይነት ይዞ ይገኛል።