ቅዳሜ 4 ኤፕሪል 2015

ስነ ልቦናዊ ሂስ

ስነ ልቦናዊ ሂስ በ “ራህማቶ” ረጅም ልቦለድ
መግቢያ
በዚህ አጭር ጽሑፍ የስነ ልቦናዊ ሂስ ምንነት፣ የስነ ልቦናዊ ሂስ መርሆዎችና የመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ። በአሰፋ ጉያ በ2002 ዓ.ም የታተመዉን “ራህማቶ” የተሰኘዉን ረጅም ልቦለድ መጽሐፍም ከተለያዩ የስነ ልቦናዊ ቲወሪዎች አንፃር ለመገምገም ሙከራ ይደረጋል። የመጽሐፉን አጽመ ታሪክ በማዉጣትና በታሪኩ ላይ የቀረቡ መረጃዎችን በመጠቀም የገጸ ባህሪያት ስነ ልቦና እንዴት እንደቀረበ ለመፈተሽ ሙከራ ይደረጋል። በመጨረሻም ከመጽሐፉ የተወሰዱትን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ማጠቃለያ የሚሰጥ ይሆናል።

የስነ ልቦናዊ ሂስ ምንነት
ስነ ልቦናዊ ሂስ በሲግመንድ ፍሩድ የስነ ልቦና መርሆዎች ላይ የተመሰረተ የሂስ አይነት ነዉ። የስነ ልቦና ንድፈ ሀሳብንና መርሆዎችንም መሰረት ያደርጋል። ይህ የስነ ጽሑፋዊ ሂስ የገጸ ባህሪያትን ዉስጣዊ ማንነት፣ ዝንባሌ፣ ፍላጎት እና ባህሪ ከስነ ልቦና አንፃር ይተነትናል። ገጸ ባህሪዉ ለሚያደርገዉ ድርጊት እና ለሚያስበዉ ሀሳብ መንስኤ የሚሆን ምክናያት አለ ብሎ ስለሚያምን ስነ ልቦናዊ ትንታኔ ያደርጋል። ማለትም ገጸ ባህሪያት ለሚያደርጉት ድርጊት እና ለሚያሳዩት የባህሪ ምስቅልቅልነት መንስኤዉ ምን እንደሆነ ያጠናል። ለምሳሌ አንድ ሰዉ በጎልማሳነቱ ለሚያሳየዉ ባህሪ በልጅነቱ ወቅት በቤተሰቡም ሆነ በአካባቢዉ ገጥሞት የነበረዉ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ገጠመኝ መሰረት ሊሆነዉ ይችላል። በሌላ በኩል የልጅነት የአስተዳደግ ሁኔታ በኋላኛዉ ዘመን ለሚያሳየዉ ባህሪ መሰረት ይሆነዋል ማለት ነዉ።

በስነ ልቦናዊ ሂስ ሀያስያን የሰዉ ልጅ ከጨቅላነት እስከ ሙሉ ሰዉነት ድረስ የሚመራባቸዉ የአዕምሮ ክፍሎች (ኢድ፣ ኢጎና ሱፐር ኢጎ) እንዲሁም ስነልቦናዊ ትወራዎች መሰረት በማድረግ የሂስ ስራቸዉን በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ላይ ያካሂዳሉ።በተጨማሪም የፍሩድን የህጻናት አስተዳደግ ስነ ልቦና (ኦራል፣ አናልና ጀኒታል) ደረጃዎችን የገጸ ባህሪያትን ማንነትና ባህሪ ለመገምገም ይጠቀሙባቸዋል። በዚህ አጭር ጽሁፍም የተለያዩ ስነ ልቦናዊ ንድፈ ሐሳቦችን ወይም መርሆዎችን መሰረት በማድረግ «ራህማቶ» የተሰኘዉን ረጅም ልቦለድ ለመገምገም ይሞከራል። የሚከተሉትን የስነልቦናዊ ሂስ ጥያቄዎች መሪ በማድረግም ስነ ልቦናዊ ሂስ ይደረጋል።
  1. የገጸ ባህሪዉ አስተዳደግ ሙሉ ሰዉ ሲሆን ተገልጧል?
  2. ከስነ ልቦናዊ ጽንሰ ሀሳቦች አንፃር የገጸ ባህሪያት ዉድቀት፣ ቀዉስ እና ፆታዊ ግንኙነት እንዴት ቀርቧል?
  3. በገጸ ባህሪዉ ድርጊትና ባህሪ ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና ያሳደረበት ተፅዕኖ አለ?

የልቦለዱ አጽመ ታሪክ
በአንድ ወቅት በደብረ ዘይት ከተማ የሚኖሩ ከማልና ዘርፌ የሚባሉ ባልና ሚስቶች ነበሩ። በቆይታቸዉ ሁለት ልጆችን ቢወልዱም በህይወት አልቆዩላቸዉም። ሶስተኛ ልጃቸዉ ራህማቶ ሲወለድ ደግሞ ዘርፌ ከዚህ አለም በሞት ተለየች። ራህማቶን አባቱ ከማል በጀርባዉ እያዘለ ጎረቤታቸዉ ወይዘሮ ፋጡማ ጡት እያጠቡ አሳደጉት። ከማል የሚሰራዉ በአንድ የመስታወትና የፍሬም መሸጫ መደብር በሀምሳ ብር ተቀጥሮ ነዉ። በዚህም የተነሳ ራህማቶ፥ የልጅነት ጊዜዉን እንደ አብዛኞቹ የሰፈሩ ልጆች ጭቃ አቡክቶ፣ ዉሀ ተራጭቶ እና ከዕኩዮቹ ጋር ተላፍቶ አላሳለፈም። ይልቁንም አባቱ በተቀጠረበት ቦታ ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ መላላክ ጀመረ። በመደብሩም የቅዱሳን አማልዕክት ምስሎች ልዩ ልዩ ስዕሎችና ፖስት ካርዶች በፍሬሞች እየተንቆጠቆጡ ለሽያጭ ይቀርባሉ። ራህማቶም በህጻን ልቦናዉ እነዚህ ስዕሎች በአዕምሮዉ ተቀረጹበት። ባገኘዉ ነገር ላይም የሚያያቸዉን ስዕሎች አስመስሎ ለመሳል ጥረት ያደርግ ጀመር። ከጊዜ ወደጊዜ እድሜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለስዕል ጥበብ ያለዉ ፍቅርም እየጠነከረ ሄደ። ምኞቱን ለማሳካትና የስዕል ጥበብ ፍቅሩን ለማርካት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘዉ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ተማሪ ለመሆን በቃ። ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ የተዋወቀዉ የቅርብ ጓደኛዉ ኬሎ ደግሞ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ተማሪ ነዉ።

ራህማቶ ለሁለት ዓመታት የስነ ጥበብ ትምህርት መማሩ ለስዕል ያለዉን ፍቅር አስታግሶለት ይሁን ሌላ ፍቅር ተጨምሮበት የስነ ጽሑፍ ፍቅር አደረብኝ በማለት ሥነ ጽሑፍ ለመማር ወሰነ። ዉሳኔዉንም አፀናዉ ተገበረዉም። ሁለት ዓመትም ሆነዉ። ጓደኛዉ ኬሎ ደግሞ ለመመረቅ አምስት ወራት ብቻ ቀርተዉታል። ራህማቶ ለስዕል ያለዉ ፍቅር እንደገና አገረሸበትና የስነ ጽሑፍ ትምህርቱን አቋርጦ የስዕል ስራ ለመስራት ወሰነ። ኬሎም ቢመክረዉ ቢመክረዉ አልመለስለት ስላለ የስዕል ስራዉን ለመጀመር የሚያስችሉትን ቁሳቁሶች ለዉድ ጓደኛዉ ለማሟላት ምኞት አደረበት።

ኬሎ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከፍተኛ ዉጤት በማምጣት ስላጠናቀቀ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆኖ የመቅረት ዕድል አጋጠመዉ። ለራህማቶም እንደተመኘዉ የስዕል ስራዉን የሚጀምርበትን ሁኔታ አመቻቸለት። ራህማቶ ስራዉን ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ስዕሎቹን ለኤግዚቢሽን አቀረበ። ለተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም ማከፋፈል ጀመረ። አድናቂና ገዥ ግን አልተገኘም። ይሁን እንጂ ራህማቶ ለስዕል ያለዉ ፍቅር አልቀነሰም። ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ደግሞ አንድ ማርታ የምትባል የ11ኛ ክፍል ተማሪ ያፈቅራል፡፡ ፍቅር የነበረዉ በሁለቱም ወገን በኩል ስለነበረ ሁለቱም ተስማሙ። ማርታ ትምህርቷን አቋርጣ ከቤተሰቦቿ ፈቃድ ዉጭ ከራህማቶ ጋር መኖር ጀመረች። ራህማቶም የስዕል ስራዉን ቀጠለ። ነገር ግን ገዥ ማግኘት ባለመቻሉ መሰረታዊ ፍላጎታቸዉን እንኳ ማሟላት አልቻሉም። ርዳታ የሚያደርግላቸዉ ኬሎ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኬሎ ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄደ። ራህማቶ በኪነ ጥበብ ፍቅርና በማርታ ፍቅር ተሰቃየ። ሁለቱን በአንድ ላይ ለማስኬድ ተቸገር። ሙያዉን ሲያፈቅር ማርታ ታኮርፋለች፤ ማርታን ሲያፈቅር ብሩሹ ታኮርፋለች። ይህ ሁኔታ ለራህማቶ ጥሩ አልሆነለትም።

ማርታ ራህማቶ ለስዕሉ የሚሰጠዉ ፍቅር ለእርሷ ከሚሰጣት ፍቅር እየበለጠ ታያት። አብረዉ ተኝተዉ ትቷት ስዕል ለመሳል ይነሳል። የምታደርገዉ አጣች። ይባስ ብሎ አንድ ቀን ሌሊት ሁለቱም በፍቅር ዉቅያኖስ ሰምጠዉ እየዋኙ እያሉ ራህማቶ ድንገት የስዕል ፍቅሩ ያይልበትና ከማርታ እቅፍ ተስፈንጥሮ ወጥቶ ሌሊቱን ስዕል በመሳል አነጋዉ። ማርታ ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዐይኗ ሳይዞርባት በንዴት ስትናጥ አደረች። ራህማቶ ሊነጋ ሲል መጥቶ ከአልጋዉ ላይ ጋደም ሲል እንቅልፍ ወሰደዉ። ማርታ ለራህማቶ ካላት ጽኑ ፍቅር የተነሳና ለስዕሎቹ እያለ እርሷን የዘነጋት ስለመሰላት ቡሩሹን ሰባበረች፤ በወረቀት ላይ የሳላቸዉን ስዕሎች ቀዳደደች፤ በጨርቅ የተሳሉትንም እንዲሁ አደረገች፤ በእንጨት ላይ የተሳሉትንም ሰባበረቻቸዉ። ራህማቶ ከዕንቅልፉ ሲነሳ የሆነዉን ሁሉ ለማመን ተቸገረ፡፡ እየቆየ ግን እዉነትነቱን እየተረዳ ሄደ። በዚህም የተነሳ በሁለቱ ፍቅረኛሞች መካከል ቅራኔ ተፈጠረ። ብዙም መጠጥ የማያዘወትረዉ ራህማቶ በሁኔታዉ የተነሳ እስከሚሰክር መጠጣት እምሽቶ መምጣት ጀመረ። ይባስ ብሎም ከአራት ቀን በሁላ በዚያዉ ማደር ጀመረ። ማርታ ይበልጥ ተናደደች። የምታፈቅረዉ ሰዉ ፍቅር እየሰጠችዉ እርሱ ፍቅር አለመስጠቱ የባሰ አንገበገባት።

ማርታ በሁኔታዎች ሁሉ አለመጣጣም የምታደርገዉ አጣች። ብዙ ካወጣች ካወረደች በኋላ ራሷን ለማጥፋት ወሰነች። ራሷንም እንደምታጠፋ ለራህማቶ ደብዳቤ ጽፋ በቀላሉ ሊመለከተዉ በሚችለዉ ቦታ ከአልጋዉ ላይ አስቀምጣለት ሄደች። በዕለቱ ራህማቶ ራሱን ስቶ በመጠጥ የዛለ ሰዉነቱን እየጎተተና እየተንገዳገደ በጊዜ ወደ ቤቱ መጣ። ማርታ በማለት በተደጋጋሚ ቢጣራም መልስ የሚሰጠዉ አላገኘም። እርሱም ለመልሱ ሳይጨነቅ ከመጠን በላይ ጠጥቶ ስለነበረ ከአልጋዉ ላይ ዧ ብሎ ወደቀ።  ስካሩ በመጠኑ በረድ ሲልለትና ሰዉነቱ መነቃቃት ሲጀምር ከመኝታዉ ተነስቶ ማርታን ፈለጋት። ግን ሊያገኛት አልቻለም። ቆም ብሎ አካባቢዉን ሲቃኝ የተጨማደደች ወረቀት ከአልጋዉ ላይ ተመለከተ። ወረቀቷን ካለችበት አንስቶ ማንበብ እንደጀመረ ከቤቱ ወጥቶ ወደ አራት ኪሎ በረረ። እየሮጠ እንዳለ ቆም ብሎ ሲመለከት ወረቀቱ ከእጁ የለም። ወደ ኋላ ወደ ፊት እየተመላለሰ ወረቀቱን ቢፈልገዉ ሊያገኘዉ አልቻለም። በዚች ዕለት ማርታንም ደብዳቤዋንም ተነጠቀ። ሁለቱንም ፍለጋ እንደወጣ ቀረ። ራህማቶም ከዚያች ቀን ጀምሮ በመላ አራት ኪሎ እብድ እንደሆነ ታወቀ። ህመሙም የሚነሳበት በምሽት ስለሆነ «ራሚ የምሽት ታማሚ» የሚል ቅፅል ስም ተሰጠዉ። ራህማቶ ቀን በሰላም ይዉላል ምሽት ያገኘዉን ወረቀት ሁሉ ይሰበስባል።

ይህ ሁሉ በሆነ አንድ ዓመት ከሁለት ወር በኋላ ኬሎ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። የራህማቶን ሁኔታ አወቀ። ከልቡም አዘነ። ዉድ ጓደኛዉን የተሰበረ ልቦናዉን ጠግኖ ቀድሞ ወደ ነበረበት ማንነቱ ለመመለስ ለራሱ ቃል ገባ። ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ራህማቶ ወደ ቀድሞዉ ሰባዊነቱ ለመመለስ በቃ። ማርታም ባልተጠበቀ ሁኔታ በህይወት ተገኘች።


«ራህማቶ» ከስነልቦናዊ ሂስ አንፃር
በዚህ ርዕስ ስር በገጽ አንድ ላይ የቀረቡትን የስነልቦናዊ ሂስ ንድፈ ሐሳቦች መሰረት በማድረግ የልቦለዱ ገጸ ባህሪያት ለሚያከናዉኑት ተግባርና ለሚያሳዩት ባህሪ ምን ስነ ልቦናዊ ምክናያት እንደሚኖር እያንዳንዱን ገጸ ባህሪ በዝርዝር ለመመልከት ሙከራ ተደርጓል።

የልቦለዱ ዋና ገጸ ባህሪ ራህማቶ የተለያዩ ባህሪያትን ሲያሳይና የተለያዩ ተግባራትን ሲፈፅም ይስተዋላል። ለምሳሌ ራህማቶ ከሚያሳየዉ ባህሪ መካከል ከፍተኛ የሆነ የስዕል ፍቅር አለበት። በገጽ አንድ ላይ ስለ ስነ ልቦናዊ ሂስ ምንነት ባነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ደግሞ ሰዎች በኋላ ላይ ለሚያሳዩት ባህሪ የልጅነት አስተዳደጋቸዉ እንደሚወስነዉ አንስተን ነበር። ራህማቶም ይህ የስዕል ጥበብ ፍቅሩ ያደረበት ያለ ምክናያት አይደለም። በልቦለዱ አጽመ ታሪክ ላይ እንደተገለጸዉ የራህማቶ አባት የሚሰራዉ በስዕልና በፖስት ካርድ መሸጫ መደብር በመሆኑና ራህማቶም እነዚያን ስዕሎች እየተመለከተ በማደጉ የተነሳ ነዉ። ራህማቶ ከአምስት ዓመቱ ገደማ ጀምሮ በዚሁ መደብር መላላክ ስለጀመረና የተለያዩ ስዕሎችንም ስለሚመለከት ከፍተኛ የሆነ አስመስሎ የመቅረጽ ፍላጎት አደረበት። ባገኘዉ ነገር ላይ ሁሉ የሚያያቸዉን ስዕሎች አስመስሎ ለመሳል ሙከራ ያደርግ ጀመር፡፡ ይህ የስዕል ጥበብ ፍቅሩ ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ ሙሉ ሰዉነቱ ድረስ አብሮት ዘለቀ። በፍሩድ የስነልቦና መርሆዎች መሰረትም የገጸ ባህሪዉ አስተዳደግ በገጸ ባህሪዉ ተግባር ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደቻለ ይሳያል።

ራህማቶ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ከጓደኞቹ ጋር ደብለቅ ብሎ ከመጫዎት ይልቅ ብቻዉን ገለል ብሎ በመቀመጥ በሀሳብ መዋተት ያዘወትር ነበር። ይህን የሚያደርገዉም እናቱ እሱን በወለደች ጊዜ እንደሞተች ስላወቀ በእኔ ምክናያት ህይወቷን አጣች እያለ ስለሚያስብና ያለ እናት ስላደገ ዉስጡን የደስተኝነት ስሜት ሊሰማዉ ስላልቻለ ነዉ። ይህም ገጸ ባህሪዉ ለሚያሳየዉ ባህሪ ምክናያት የሆነዉ ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ነዉ።

ራህማቶ የባህሪ ምስቅልቅልነትም ይታይበታል። በአንድ አላማ ላይ አይጸናም። ለዚህ ባህሪዉም ምክናያት አለዉ። ራህማቶ መጀመሪያ የስዕል ፍቅር አደረበት። ቀጥሎ የስነ ጽሑፍ ፍቅር ተጠናወተዉ። በመጨረሻም ከማርታ ጋር ፍቅር ጀመረ። ራህማቶ በአንድ በኩል በኪነ ጥበብ ፍቅር በሌላ በኩል ደግሞ በማርታ ፍቅር ይዋትታል። አንዱን ለመምረጥም ይቸገራል። የኪነ ጥበቡንም የማርታንም ፍቅር ጎን ለጎን ለማስኬድ ሞከረ አልተሳካለትም። ለዚህ የባህሪ ምስቅልቅልነቱም ምክናያት አለዉ። ይኸዉም ከላይ እንደተገለጸዉ ለጥበብ ያለዉ ፍቅር ከአስተዳደጉ ጋር በተያያዘ የመጣ ሲሆን ለማርታ ያለዉ ፍቅር ደግሞ በስነ ልቦና ምሁራን ዘንድ የሰዉ ልጅ የስነ ልቦናዊ አስተዳደግ ደረጃዎች ተብለዉ የሚታወቁት ነገሮች የፈጠሩት ተፅዕኖ ነዉ። ለምሳሌ በፍሩድ የህጻናት አስተዳደግ ስነ ልቦና መሰረት የህጻናት የዕድሜ ክልል በተለያየ ቁጥር የመደሰቻ አጋጣሚዎችም እየተለያዩ ይሔዳሉ። ህጻናት «ኦራል» ደረጃ ላይ ሲሆኑ የሚያስደስታቸዉ ቃላዊ የሆነ ነገር ሲሆን «አናል» በሚባለዉ ደረጃ ላይ ደግሞ ከመጸዳዳት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ይደሰታሉ። «ጀኒታል» ላይ ሲደርሱ ደግሞ የሚደሰቱት ከተቃራኒ ፆታ ጋር በሚኖራቸዉ ግንኙነት ነዉ። ስለሆነም ራህማቶ ከማርታ ጋር ፍቅር የጀመረዉ  በዚህ የሰዉ ልጆች አስተዳደግ ስነ ልቦና መሰረት የሚገኘዉ «ጀኒታል» ደረጃ ላይ በመሆኑ ነዉ። በእነዚህ በሁለቱ ፍቅር በመዉደቁ የተነሳ የባህሪ ምስቅልቅልነት ሊደርስበት ችሏል፡፡

ራህማቶ የማርታና የጥበብ ፍቅሩ ይጋጩበትና ሁለቱን ማስኬድ ከባድ ይሆንበታል። በሁኔታዉም የተነሳ ለዕብደት ይዳረጋል። ዕብድነቱም ተረጋግጦ «ራሚ የምሽት ታማሚ» ተብሎ በመላ አራት ኪሎ ታወቀ። ራህማቶ ህመሙ የሚነሳበት ምሽት ላይ ነዉ። ህመሙ በሚነሳበት ወቅት የሚተገብረዉ ተግባር ደግሞ የወዳደቁ ወረቀቶችን ሁሉ መልቀም ነዉ። ከስነ ልቦናዊ ሂስ አንፃር ራህማቶ ለሚተገብራቸዉ ተግባራት ሁሉ ምክናያት አለዉ። ይኸዉም ህመሙ ምሽት ላይ የሚነሳበት ማርታ ራሷን ልታጠፋ እንደሄደች ያወቀ በምሽት በመሆኑ ምሽት ላይ ቢፈልጋት የማገኛት  እየመሰለዉ ሲሆን፣ የወዳደቁ ወረቀቶችን የሚለቃቅም ደግሞ ማርታ ጽፋለት የሄደችዉን ደብዳቤ ሙሉ በሙሉ ሳያነበዉ ከዕጁ ስለጠፋዉ የማገኘዉ እየመሰለዉ ያገኘዉን ወረቀት ሁሉ ይሰበስባል።

ሌላኛዋ ገጸ ባህሪ ማርታ ከስነ ልቦናዊ ሂስ አንፃር ስትታይ የሰዉ ልጅ ከሚመራባቸዉ የአዕምሮ ክፍሎች መካከል የ«ኢድ»ን ተግባር በተደጋጋሚ ስትፈጽም ትስተዋላለች። እንደ ፍሩድ አተያይ «ኢድ» በምንም ተፅዕኖ ስር ሳንወድቅ ለምክናያት ሳንጨነቅ የሚያስደስተንን ነገር ሁሉ እንድንፈጽም የሚገፋፋን ክፍል ነዉ። ደመነፍሳዊ የሆነ ሀሴትንም የሚፈልግ ነዉ። ማርታም የምትተገብራቸዉ ተግባራት ምክናያታዊ ሳይሆኑ ከ«ኢድ» የመነጩና ደመ ነፍሳዊ ሀሴትን የሚፈልጉ ናቸዉ። ለምሳሌ ከቤተሰቦቿ ጠፍታ ወደ ራህማቶ ስትሄድ ለርሱ ያላትን ፍቅር ለማስታገስ ብቻ እንጂ ስለ ቤተሰቦቿ ያሰበችዉ ነገር የለም። ከራህማቶ ጋር በምትኖርበት ወቅትም የራሷን የዉስጥ ፍላጎት ብቻ በማዳመጥ በኋላ ለሚከሰተዉ ነገር ባለመጨነቅ የራህማቶን ብሩሽ ሰበረች። ስዕሎችንም አበላሸች። ይህን ሁሉ ያደረገችዉ ግን የሚትፈልገዉን የራህማቶን ፍቅር ለማግኘት ስትል ነዉ። ዳሩ ግን ይህ ተግባሯ ከራህማቶ ጋር የበለጠ አራራቃቸዉ እንጂ አላቀራረባቸዉም። ምናልባትም የ«ኢጎ» ጣልቃ ገብነት ቢኖር ኖሮ ማርታ ፍቅሯን ከማጣት ራህማቶም ከዕብደት ሊድኑ ይችሉ ነበር። ምክናያቱም «ኢጎ» ምክናያታዊ ነዉና ማርታ ይህን ብፈጽም ይህ ይከሰትብኛል የሚል ምክናያታዊ የሆነ ጥያቄ አዕምሮዋ ሊያመነጭ ይችል ነበር። ሆኖም የ«ኢድ» ፍላጎት አየለና ለሁለታቸዉ መለያየት ምክናያት ሊሆን ቻለ።

ማርታ ራሷን ለማጥፋት ያሰበችም ያለምክናያት አይደለም። ራህማቶ በኪነ ጥበብ ፍቅር ተተብትቦ እርሷን የተዋትና የጠላት ስለመሰላት ነዉ። በተጨማሪም ራህማቶ ቢተዋት ቀደም ከቤተሰቦቿ ፈቃድ ወጥታ ስለመጣች የምትጠጋበት እንደሌላት እየታወሳትና አባቷ መሞታቸዉን በመስማቷ በዉስጧ የተሰነቀረዉ ሀዘን አላስችል ብሏት ነዉ። ይህን ሁሉ ስታስበዉ የወደፊት ህይወቷ ጨለማ መስሎ ስለታያት ራሷን ለማጥፋት ወሰነች።

ማጠቃለያ
በዚህ ጽሑፍ በ «ራህማቶ» ረጅም ልቦለድ ዉስጥ ያሉ ገጸ ባህሪያት ስነ ልቦና ምን እንደሚመስል ለማየት ተችሏል። በተለይ ሁለቱ ገጸ ባህሪያት የሚያሳዩትን ባህሪና የሚፈጽሙትን ድርጊት ከተለያዩ የስነ ልቦናዊ ሂስ ንድፈ ሐሳቦች አንፃር ለመመልከት ተችሏል። ለምሳሌ ዋናዉ ገጸ ባህሪ ራህማቶ ከፍተኛ የሆነ የኪነ ጥበብ ፍቅር አለበት። ደስተኛነት ብዙም አይሰማዉም። የባህሪ ምስቅልቅልነትም ይታይበታል። በተጨማሪም በአዕምሮዉ ዉስጥ ስነ ልቦናዊ ግጭት ይስተዋልበታል። ለእነዚህ ባህሪያቱና ድርጊቱ ደግሞ ስነ ልቦናዊ የሆነ ምክናያት አለዉ። ለስዕል ያለዉ ፍቅርና ደስተኛ አለመሆኑ አስተዳደጉ ከፈጠረበት ተፅዕኖ የመነጨ ሲሆን የሚያሳየዉ የባህሪ ምስቅልቅልነት ደግሞ በዉስጡ ካለዉ የፍላጎት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ የመጣ ነዉ።

ማርታንም ከስነልቦናዊ ሂስ አንፃር ስንመለከታት የሚያስደስታትን ነገር ሁሉ ከመተግበር ወደ ኋላ አትልም። ይኸዉም «ኢድ» ከሌሎች የአዕምሮ ክፍሎች ከፍተኛ ድርሻ በመዉሰዱ ነዉ። ለዚህም ነዉ ማርታ የራህማቶን ቡሩሽ የሰበረችና ስዕሎቹን ያበላሸች።

በአጠቃላይ በተደረገዉ የስነ ልቦናዊ ሂስ ስራ በልቦለዱ ዉስጥ ያሉት ገጸ ባህሪያት ለሚያሳዩት ባህሪና ለሚተገብሩት ተግባር የአስተዳደግ ሁኔታቸዉና የተለያዩ ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ምክናያት እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም የገጸ ባህሪያት ፆታዊ ግንኙነት ከሰዉ ልጅ የአስተዳደግ ስነ ልቦና ንድፈ ሐሳቦች አንፃር ምን እንደሚመስል ታይቷል።